በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የሚገኘው የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ለእርሻ ኢንቨስትመንት በመሰጠቱ ከ200 ሄክታር በላይ የፓርኩ መሬት ደን ሙሉ ለሙሉ መውደሙን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የብሔራዊ ፓርኮች አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አዳነ ጸጋዬ፤ የባቢሌን የዝሆኖች መጠለያ ፓርክ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በኩል ለእርሻ ኢንቨስትመንት ተሰጥቶ ፓርኩ እየታረሰ በመሆኑ፣ በፓርኩ የሚገኙ ዝሆኖች ለአደጋ ተጋልጠዋል ብለዋል፡፡
የባቢሌን የዝሆኖች መጠለያ በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች ድንበር ላይ የሚገኝ ሲሆን “በኦሮሚያ ክልል በኩል ያለው የፓርኩ ክፍል ለኢንቨስትመንት በመሰጠቱ አሁንም ድረስ እየታረሰ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
የፓርኩ መሬት ለኢንቨስትመንት የተሰጠው ፓርኮችን ለመጠበቅና ለማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን በማያውቅበት መንገድ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ሥራ አስፈጻሚው አክለውም “ከኹለት ወር በፊት ከኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ተወካይ ጋር በመሆን የፓርኩ ይዞታ እንዳይነካ አካለን የተመለስን ቢሆንም፤ ከዚያ ወዲህ ባሉት ጊዜያት የፓርኩ ውስጣዊ ክፍል እየታረሰ ነው” ብለዋል።
“ጉዳዩን እንደሰማን ባለፈው ነሐሴ ወር ወደ ቦታው ሄደን ያየነው ነገር እጅግ አሳዛኝ ነው” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አክለውም “የዝሆኖች መጠለያ ከባድ ጉዳት እየደረሰበት ነው፤ በርካታ የእርሻ ማሽኖች የፓርኩ ክልል ገብተው እያረሱ ነው፡፡ በየቀኑ እየወደመ ያለውን የፓርኩ ክፍል ልገልጽልህ አልችልም” ብለዋል፡፡
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፓርኩን የመጠበቅ ኃላፊነቱን ወደ ጎን በመተው ያለእኛ እውቅናና ፈቃድ ለእርሻ ኢንቨስትመንት በሚል ለባለሀብቶች ከፓርኩ መሬት ሰጥቷል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪን የሚመለከተው አካል ተወያይቶ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ በፓርኩ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት እንዲቆም ቢጠይቅም፤ “ለሰከንድ አናቆምም” የሚል ምላሻ ሰጥተዋል ነው ያሉት።
የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ፓርክ በአለም አቀፍ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሕብረት የተመዘገበ እና ከሦስት መቶ በላይ ዝሆኖች እና የተለያዩ የዱር እንስሳትን የያዘ መጠለያ ነበር፡፡