የአፍሪካ ልማት ባንክ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሃይል አቅርቦትን ለማሻሻል የሚያግዝ የ104 ሚሊዮን ዶላር ፈንድ ማጽደቁን ገልጿል።
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ያጸደቀው የገንዘብ ድጋፍ 52 ሚሊዮን ዶላሩ ከአፍሪካ ልማት ፈንድ የተገኘ መሆኑም ተመላክቷል።
ቀሪው የገንዘብ ድጋፍ ደግሞ የባንኩ የብድር አጋር ከሆነው በኮሪያ-አፍሪካ የኢነርጂ ኢንቨስትመንት ማዕቀፍ ስምምነት ከኮሪያ የኢኮኖሚ ልማት ትብብር ፈንድ የተገኘ እንደሆነ ተገልጿል።
የባንኩ የኃይል ሥርዓት ልማት ዳይሬክተር ባቺ ባልዴህ፤ ፕሮጀክቱ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ያለውን የኃይል ቋት አቅም በማሳደግ ታዳሽና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
መንግሥት በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚያደርጋቸውን የኃይል አቅርቦት ጥረቶች የሚያግዝ ሲሆን፤ አርብቶ አደሮች፣ አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮችና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ 157 ኪሎ ሜትር እርዝማኔ ያለው የ400 ኪሎ ቮልት ባለ ኹለት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን እና ተያያዥ ማከፋፈያ ጣቢያዎችን በሐረር፣ በጅግጅጋ እና በፋፈም የሚደረጉ ግንባታዎችን ያካተተ መሆኑም ተጠቁሟል።
ግንባታው ሲጠናቀቅም በምሥራቅ የኢትዮጵያ ክፍል ያለውን የኃይል ማስተላለፊያ አቅም እንደሚያሳድግ ይጠበቃል ተብሏል።
ፕሮጀክቱ በቀጣይ ከሶማሊያ ጋር የኃይል ትስስር ለመፍጠር እንደ መነሻ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፤ ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ምጣኔ ኃብታዊ ውህደትን በማሳለጥና ንግድን በማቀላጠፍ ረገድ አስተዋፅኦ ያደርጋልም ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ መንግሥት በክልሉ በ462 ሺሕ ሄክታር መሬት ላይ ለምግብ ዋስትናና ለእንስሳት መኖ ልማት እየተገበረው ያለውን ግዙፍ የመስኖ ሥራ እንደሚያግዝ ተገልጿል።