የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በተያዘው ዓመት ውስጥ 42 ቢሊየን ብር ገቢ አግኝቻለሁ ያለ ሲሆን ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቋል።
ተቋሙ በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ማቀዱን አመልክቷል።
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) እንዳሉት ኮቪድ 19፣ የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት፣ የሀገር ውስጥ ፀጥታ ችግርና ሌሎች ችግሮች በድርጅቱ ስራዎች ላይ ተፅዕኖ ነበራቸው።
በበጀት ዓመቱ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ከተጓጓዘው 7 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን እቃ ውስጥ 34 በመቶውን የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ማጓጓዙን ገልጸዋል።
በመርከብ የወጪ ጭነትና ጥቅል ጭነት አገልግሎት በእቅዱ ልክ መፈፀሙን ጠቅሰው፣ በብረት ማጓጓዝ ረገድ ግን ዝቅተኛ አፈፃፀም እንደነበር አንስተዋል።
ተጨማሪ 185 መኪናዎች በመግዛት ከጅቡቲ-አዲስ አበባ ዕቃ የማጓጓዝ ስራዎችን ከእቅድ በላይ ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
በዩኒሞዳልና በመልቲ ሞዳል፣ በወደብና ተርሚናል አገልግሎት፣ በወጪ ዕቃ ማጓጓዝ፣ በመጋዘን አገልግሎት በአብዛኛው ከእቅዱ በላይ መሳካቱንም ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሁለት ወር በፊት ከ60 ሺህ ቶን በላይ እቃ የመጫን አቅም ያላትን መርከብ መረከቧ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በቅርቡ ባህር ዳር እና ሀዋሳ የተሰኙ ሁለት መርከቦች ለኪሳራ ዳርገውኛል በሚል መሸጡ አይዘነጋም።
በተሸጡት ሁለት መርከቦች ምትክም አባይ የተሰኘች አዲስ መርከብ ከቻይና መግዛቱን አስታውቋል።
አዲሷ መርከብም በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ታሪክ በግዙፍነቷ አቻ የላትም የተባለ ሲሆን መርከቧ በኢትዮጵያ እጅ መግባቷን ድርጅቱ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ድርጅት በ3 ሺህ ቶን የመጫን አቅም ባላቸው መርከቦች ስራውን መጀመሩ ይታወሳል።