የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፕላን ጥገና ፈቃድ ሰጥቷል፡፡
ባለስልጣኑ ዋን ኤም. አር.ኦ (One M.R.O) ለተሰኘ የግል ተቋም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነውን አውሮፕላን ጥገና ፈቃድ ሰጥቷል፡፡
በ2013 ዓ.ም የቢዝነስ ፈቃድ አውጥቶ የተቋቋመው ዋን ኤም. አር.ኦ የጥገና ፈቃድ ሰርትፊኬት ለማግኘት የበቃው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያዘጋጃቸውን አምስት ዓለም አቀፍ መስፈርቶች አሟልቷል በሚል ነው፡፡
ለተቋሙ የተሰጠው የጥገና ፈቃድ ቦይነግ 737 ክላሲክና ቦይንግ 737 ኔክስት ጄኔሬሽን የተባሉ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን መጠገን ያስችለዋል ተብሏል፡፡
ዋን ኤም.አር ኦ. የጥራት ማረጋገጫና ደህንነት ማናጀር አቶ አንዱአለም ስለሺ ፤ ድርጅታቸው በአሁን ሰዓት ናይጄሪያ ላይ መሰረት አድርጎ በምዕራብ አፍሪካ ለሚገኙ የግል ኦፐሬተሮች የጥገና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ድርጅታቸው በቀጣይም በኢትዮጵያ የጥገና ማዕከል በመገንባት የግል አየር መንገዶች እየገጠማቸው ያላቸውን ከፍተኛ የአውሮፕላን ጥገና ችግር እንደሚፈቱም አክለዋል፡፡
አያይዘውም ወደፊት በኢትዮጵያ ለሚያደርጉት ኢንቨስትመንትም “መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግልን አምናለሁ” ብለዋል፡፡
በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ 12 የታደሰ ፈቃድ ያላቸው የግል አየር መንገዶች ያሉ ሲሆን እነሱን የሚያስተናግድ የጥገና ማዕከል ባለመኖሩ አውሮፕላን ለማስጠገን ከሀገር ውጭ ወደ ኬንያ እና አውሮፓ ሀገራት በመላክ ይጠገኑ ነበር ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የግል ኦፐሬተሮች እየገጠማቸው ያለውን የጥገና ማዕከል ችግር ለመቅረፍ የግል አየር መንገዶችን በማደራጀት እዚሁ ጥገና የሚያደርጉበትን መንገድ እያመቻቸ ነው ተብሏል፡፡