አፍሪካ ህብረት በአማራ ክልል ያለው ሁኔታ እንዳሳሰበው ገለጸ

የአፍሪካ ህብረት ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ አማራ ክልል ያለው ሁኔታ እንዳሳሰበው አስታውቋል።

ህብረቱ በመገለጫው አክሎም የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀማት ጉዳቱን እየተከታተሉት እንደሆነም ገልጿል።

ሊቀመንበሩ አክለውም በአማራ ክልል ያለውን ወታደራዊ ፍጥጫ በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑንም አስታውቋል።

አፍሪካ ህብረት ለኢትዮጵያ ህገመንግስታዊ ስርዓት፣ ሉዓላዊነት እና አንድነት ድጋፍ እንደሚያደርግም ህብረቱ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ አካላት ንጹሀንን ከጉዳት እንዲጠብቁ እና ግጭት እንዲያቆሙ ያሳሰቡት ሊቀመንበሩ ወደ ውይይት እንዲመጡ እና ችግራቸውን እንዲፈቱም አስጠንቅቋል።

ሙሳ ፋኪ አክለውም አፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ለሚደረጉ ውይይቶች ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የፌደራል መንግስት ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ላይ የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ አደራጃለሁ በማለቱ በአማራ ክልል ተቃውሞ ገጥሞታል። ይህን ተከትሎም የክልሉ መንግስት የጸጥታ ሁኔታው ከአቅሙ በላይ መሆኑን ገልጾ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቁ ይታወሳል።

በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ላሊበላ እና ኮምቦልቻ ይደረጉ የነበሩ በረራዎች ተሰርዘዋል።

በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች አሁንም በሀገር መከላከያ እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው የተባለ ሲሆን ተቋርጠው የነበሩ በረራዎች ዳግም ቀጥለዋል ተብሏል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ባሳለፍነው ሰኞ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጽድቋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *