የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን የጠቅላይ ሚንስቴር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የሕዝብን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በቀረበው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6 /2015 ላይ ነው፡፡
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የሚታየውን በትጥቅ የተደገፈ ህገወጥ እንቅስቃሴ በመደበኛ የህግ ማስክበር ስርዓት ለመቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ የተሸጋገረ በመሆኑ፤ ይህ እንቅስቃሴ የክልሉን ነዋሪ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ ያወከ እና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ፤ የሕዝብን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም ህግ እና ስርዓት ለማስከበር የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ፣ እንቅስቃሴው በሃገር ደህንነት እና በህዝብ ሰላም ላይ የደቀነው አደጋ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መጥቷል ተብላል፡፡
መንግስት ትጥቅ አንስተው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ሁሉ የሰላም እና ህጋዊ መንገድን እንዲከተሉ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ሲያደርግ እንደቆየም በነግለጫው ላይ ተጠቅሳል።
ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አክሎም የታጠቁ ሀይሎች እየፈፀሙ ባለዉ ጥቃት ምክንያት የክልሉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነውም ብሏል፡፡
የክልሉ መንግስትም በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ያጋጠመው የፀጥታ መደፍረስ በክልሉ ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያስከተለ የሚገኝ መሆኑን በመግለጽ፣ ሁኔታውን በመደበኛው የህግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ፣ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ በኢፌድሪ ህገ መንግስት መሰረት እንዲደነግግ እና ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ጥያቄ አቅርቧል ተብላል።
በመደበኛ የህግ ስርዓትን መሰረት አድርጎ ይህን ፈር የለቀቀ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር አዳጋች ሁኔታ በመፈጠሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘ ተገልጻል።
ህገመንግስቱ እና ህገመንግስታዊ ስርዓት ላይ የተቃጣ አደጋን በመደበኛ የህግ ስርዓት ለመቆጣጠር ባልተቻለ ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ህገመንግስታዊ ስርዓትን ከአደጋ የመከላከል ስልጣን እንዳለው በኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀፅ 93 (1) ተደንግጓል ተብላል፡፡
በመሆኑም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በህገመንግስቱ የተጣለበትን ሃላፊነት ለመወጣት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ስላለበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 እንዲታወጅ በሙሉ ድምጽ መወሰኑ ተገልጿል።
ይሁንና በአማራ ክልል የተወሰነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አልተገለጸም።
በህገ ሙንግስቱ ድንጋጌ መሰረት የሚንስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ ስልጣን ያለው ቢሆንም ውሳኔው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በአብላጫ ድምጽ መጽደቅ እንዳለበት ያስቀምጣል።