ኢትዮጵያና የአለም ባንክ ለሰው ሀብት ልማት አገልግሎት የሚውል የ400 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነት በበይነ መረብ በተካሄደ ሥነ-ስርዓት ተፈራርመዋል፡፡
በስምምነቱ ከተፈረመው 400 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 350 ሚሊዮን ዶላር የልማት ድጋፍ ሲሆን 50 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ብድር መሆኑ ታውቋል፡፡
የፋይናንስ ድጋፉ ለሰው ሀብት ልማት ማለትም የትምህርትን ጥራትንና ውጤታማነትን ለማሻሻልና የስርዓተ ምግብን አገልግሎት ለማጎልበት የሚውል ሲሆን፤ ከአገልግሎቱም በመላ አገሪቱ የሚገኙ ልጃገረዶችና ታዳጊ ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሰው ሀብት ልማት አገልግሎቱ በግጭትና ድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን የሚያካትት ሲሆን፤ የማህበራዊ አገልግሎቶች አሰጣጥን ለማጠናከርና ተጠያቂነትን ለማስፈንም አስተዋጽዖ እንዳለው ተነግሯል፡፡
የፋይናንስ ድጋፉ ውጤታማ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማረጋጋጥ የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ በተመረጡ ወረዳዎች የስርዓተ ምግብ አገልግሎትን በማጎልበት የህጻናት መቀንጨርን ለመከላከል እንደሚረዳ ታምኖበታል፡፡
የገንዘብ ድጋፉ ጥራት ያለው የማህበራዊ አገልግሎትን ለማህበረሰቡ ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ በዘርፉ ለተሰማሩ አስፈጻሚዎችና ባለሙያዎች ቴክኒካዊ የአቅም ግንባታ ድጋፍ በማድረግም ውጤታማነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ለሰው ሀብት ልማት ቅድሚያ የምትሰጥና ለተግበራዊነቱም የላቀ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች የምትገኝ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ ከጁላይ 25-26 / 2023 በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም በተካሄደው የሰው ሀብት ልማት የመሪዎች ጉባኤም ድጋፍና ቁርጠኝነቷን አረጋግጣለች፡፡
የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የፈረሙ ሲሆን፤ በአለም ባንክ በኩል ሚስተር ኦስማን ዲዮን በአለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ተጠሪ መፈረማቸው ተገልጿል፡፡