ኢትዮጵያ 12 ቢሊዮን ዶላር ብድር እንዲሰጣት ጠየቀች

የኢትዮጵያ መንግስት ለሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ 12 ቢሊዮን ዶላር ብድር ጠይቋል፡፡

ብድሩ እና እርዳታው የተጠየቀው የዓለም የገንዘብ ድርጅት አይኤምኤፍ፣ ዓለም ባንክና ኢትዮጵያ ያለባትን የውጭ ዕዳ መልሶ ከማሸጋሸግ ለማግኘት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ለሪፖርተር እንዳሉት ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከአሜሪካ፣ ፈረንሣይና ሌሎች ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት መልካም መሆኑ ብድሩ ሊገኝ ይችላል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲስተካከል ጠይቃለች ያሉት አማካሪው ብድሩ ድርድር ከተደረገበት በኋላ ይለቀቃል የሚል ተስፋ መኖሩንም ጠቅሰዋል፡፡

የአሜሪካ ኮንግረስ ኢትዮጵያ ላይ ጥሎት የነበረውን ገደብ እ.ኤ.አ. በጁላይ ወር መጨረሻ ላይ ያነሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ ይህም ገንዘቡን ለማግኘት ጥሩ እርምጃ ይሆናልም ተብሏል፡፡

12 ቢሊዮን ዶላሩን ለማግኘትም ወሳኝ የሆነ ድርድር በቅርቡ እንደሚጀመር የገለጹት አቶ ተክለ ወልድ፣ የመጨረሻ ወሳኔ ላይ የሚደረሰውም ድርድሩ በሚያስገኘው ውጤት መሠረት ይሆናልም ብለዋል፡፡

ገንዘቡን ለማግኘት ኢትዮጵያ ከተቋማቱ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማስተናገድ በሚያስችል ደረጃ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ድርድር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

 የአለም ባንክ እና አይኤምኤፍ ኢትዮጵያ የጠየቀችውን ገንዘብ የተያዘው 2023 ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት ሊለቁ እንደሚችል ይጠበቃል ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ 28 ቢሊዮን ዶላር የውጭ እዳ እንዳለባት ብሔራዊ ባንክ ያስታወቀ ሲሆን ከፍተኛ የብድር ጫና ካለባቸው ሀገራት መካከልም አንዷ ነች፡፡

የአለም ባንክ እና አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ ብድር ከመፍቀዳቸው በፊት ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀመጡ ሲሆን የመጀመሪያው የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም፣ የጥቁር ገበያ ውጪ ምንዛሬ በባንክ በኩል ከሚካሄደው ጋር እኩል ማድረግ ዋነኞቹ ናቸው፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *