የትምህርት ሚኒስቴር በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናን ወስደው ወደ ዩንቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎችን የሬሚዲያል ፕሮግራም በመስጠት ለይ መሆኑ ይታወሳል፡፡
እነዚህ ተማሪዎች ከትናንት ሰኔ 26 ቀን ጀምሮ የ12ኛ ክፍል ፈተናን በያሉበት ሆነው በመፈተን ላይ ናቸው፡፡
ይሁንና ሚኒስቴሩ ይህ ፈተና መሰረዙን ያስታወቀ ሲሆን ምክንያቹን ከመናገር ተቆጥቧል፡፡
በፈተና ሂደት በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት የትምህርት ሚኒስቴር ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ.ም የተሰጡት የሬሜዲያል ፕሮግራም ፈተናዎች ተሰርዘው ተማሪዎች በቀሩት የትምህርት ዓይነቶች ብቻ እንዲመዘኑ መወሰኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
እንዲሁም ቀደም ብሎ በሁሉም ሬሜዲያል ፕሮግራም ተጠቃሚ ተማሪዎች ባላቸው ተቋማት ፈተናውን በአንድ ጊዜ ለመስጠት የታቀደው ፕሮግራም ማሻሻያ እንደተደረገበትም ገልጿል፡፡
በተለይም ከ150 በላይ የሆኑና ከ200 በላይ ካምፓስ ያላቸውን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈተና ቀርቶ ወደ ፊት በሚወሰን አግባብ ፈተናው በመስከረም ወር 2016 ዓ.ም ይሰጣልም ብሏል፡፡
ይሁንና በመንግስት ተቋማት የሬሜዲያል ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆኑትን ተማሪዎች በተያዘላው ፕሮግራም መሰረት እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
እንደ ትምህርት ሚንስቴር ገለጻ የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ፈተና ከሀምሌ 19 እስከ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ይካሄዳል።
በመንግሥት ዩንቨርሲቲዎች ይሰጣል የተባለው ይህ ፈተና የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ሚንስቴሩ አስታውቋል።
ከዘንድሮ ተፈታኞች መካከል 365 ሺህ 954 ያህሉ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ናቸው ተብሏል።
በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍልን ከተፈተኑ 900 ሺህ ገደማ ተማሪዎች ውስጥ ወደ ዩንቨርስቲ ማለፊያ ውጤት ያመጡት 30 ሺህ አይሞሉም መባሉ አይዘነጋም።