በኦሮሚያ ገብረ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ ከ50 በላይ ሰዎች ታገቱ

በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የታገቱትን ሰዎች ለማስለቀቅ ለእያንዳንዳቸው አንድ ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ ተጠይቀዋል

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገብረ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ ባሳለፍነው ቅዳሜ ማለዳ ላይ ከአዲስ አበባ ወደ ባህርዳር በመጓዝ ላይ የነበሩ ከ50 በላይ መንገደኞች ታይተዋል ።

እገታውን የፈጸሙት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው የተባለ ሲሆን ለአንድ ሰው አንድ ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ የታጋች ቤተሰቦች ታጣቂዎቹ እየደወሉ መጠየቃቸው ተገልጿል።

እገታው የተፈጸመበት ስፍራ ከኢትዮጵያ ዋና ከተማ 75 ኪሎ ሜትር ላይ ሲሆን የፌደራል ፖሊስም ሆነ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ታጣቂዎቹ በዜጎች ላይ እገታውን ሲፈጽሙ ማስጣል እንዳልቻለ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል ።

በዚህ አካባቢ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የሚያደርሱትን ጥቃት በመፍራት የሌሊት ጉዞ ከቆመ አንድ ዓመት እንዳለፈውም ነዋሪዎቹ ለኢትዮ ነጋሪ ተናግረዋል ።

የኦሮሚያ ክልልም ይሁን የፌደራል መንግሥት በእገታው ዙሪያ እስካሁን መግለጫ ያላወጣ ሲሆን ቤተሰቦቻቸው የታገቱባቸው ሰዎች ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ።

ኦነግ ሸኔ ከሁለት ዓመት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት መመዝገቡ ይታወሳል።

ይህ የሽብር ድርጅት በኦሮሚያ ክልል ሁሉም ዞኖች በመንቀሳቀስ በንጹሀን ዜጎች ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ ይገኛል።

የፌደራል መንግሥት ከሁለት ወር በፊት ከዚህ የሽብር ቡድን ጋር በታንዛኒያ ድርድር የጀመረ ቢሆንም ድርድሩ ያለ ስምምነት ተጠናቋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *