ኢትዮጵያን የጉዛራ ቤተ መንግሥት በ35 ነጥብ ስምንት ሚሊየን ብር ጥገና ሊደረግለት ነው

በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚገኘው የጉዛራ ቤተመንግሥት ከተደቀነበት የመፍረስ አደጋ ለመታደግ፤ ከፌደራል መንግሥት በተበጀተ 35 ሚሊዮን 800 ሺሕ ብር በጀት የጥገና ሥራው በዛሬው ዕለት እንደሚጀመር ተገልጿል።

የጥገና ሥራው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ፅ/ቤት የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ግርማቸው ሙሉጌታ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ጉዛራ ቤተመንግሥት በጣና ተፋሰስ አካባቢዎች የሚገኝ የመጀመሪያው ቤተመንግሥት እንደሆነ ይነገራል።

ጉዛራ ቃሉ የግዕዝ ሲሆን፤ ትርጉሙም ምቹ ማለት ነው። በጎንደር የነገሥታት ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የጉዛራን ቤተመንግሥት የመሰረቱትም ያሳነፁትም ኢትዮጵያን ከ1556-1589 ድረስ በመሩት በአፄ ሰርፀ ድንግል መሆናቸው በፁሁፍ የሰፈሩ ማስረጃዎች ያሳያሉ።

የጉዛራ ቤተመንግሥት ከእንፍራንዝ በስተደቡብ 5 ኪሎሜትር ወጣ ብሎ የተሰራ ግምብ ሲሆን፤ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ፣ ከጣና ሐይቅ በስተ ስሜን ምስራቅ በኩል ይገኛል።

አፄ ሠርፀ ድንግል በጉዛራ ቤተመንግሥት ከ1555 እስከ 1589 ለ34 ዓመታት ነግሰዋል። በዚህ ጊዜ የጎንደርም የጎርጎራም አቢያተ መንግስታት አልተመሰረቱም።

ከጎንደር ነገስታት የመጀመሪያው እና የጎንደር መስራችም በመባል የሚታወቁት አፄ ሠርፀ ድንግል አባታቸው አፄ ሚናስ ሲሆኑ፤ አፄ ልብነድንግልና አፄ ናኦድ ደግሞ አያትና ቅድመ አያታቸው መሆናቸው በታሪክ ይነገራል።

ከአፄ ሠርፀ ድንግል በኋላ ልጃቸው አፄ ያዕቆብ ለ7 ዓመታት፣ የወንድማቸው ልጅ ዘድንግል ለአንድ ዓመት ተኩል እንዲሁም አፄ ሱሲንዮስ ለ3 ዓመት እንደነገሱበት የታሪካቸው ስንክሳር ያትታል።

በክረምቱ ዝናብና በበጋው ፀሐይ አማካኝነት በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጉዛራ ቤተመንግሥት በተለይ በ 2012 በጣለው ዝናብ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ተነግሯል።

የጉዛራ ቤተመንግሥት ስፋቱ 12 በ 18 ሜትር ነው። ቁመቱ 16 ሜትር ሲሆን፤ በአጠቃላይ 216 ሜትር ስኩየር ስፋት አለው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *