የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት የ9 ወር የሥራ ክንውን ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል፡፡ ኮሚሽኑ ባቀረበው የሥራ ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባደራጃቸው ዘጠኝ የትኩረት መስኮች የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ የተገኙ ውጤቶች እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በዝርዝር ተካትተዋል፡፡
በቀረበው ሪፖርት የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራን በተመለከተ ኮሚሽኑ በዋናው መሥሪያ ቤቱና በከተማ ጽሕፈት ቤቶቹ በ1491 ሰዎች 1680 ጉዳዮች ላይ አቤቱታ የቀረቡለት ሲሆን ከነዚህም መካከል በኮሚሽኑ ሥልጣን ሥር የሚወድቁ 1084 አቤቱታዎችን ተቀብሎ ማስተናገዱ ተገልጿል፡፡ አቤቱታ ከቀረበባቸው ጉዳዮች መካከል አብዛኞቹ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶችን የተቀሩትደግሞ የኢኮኖሚያዊናየማኅበራዊ መብቶችንየተመለከቱ ናቸው።
ኮሚሽኑ በ48 ማረሚያ ቤቶች እና በ323 ፖሊስ ጣቢያዎች አካሄድኩት ባለው ክትትል ለይቶ ባስቀመጣቸው ግኝቶች እና በሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች መሠረት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እና ያለበቂ ማስረጃ በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎች መፈታታቸውን፣ የዋስትና መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው መደረጉን፣ ኢ-ሰብአዊ አያያዝ ሲፈጽሙ የነበሩ የተወሰኑ የጸጥታ አባላት ተጠያቂ መደረጋቸውን፣ በመደበኛ ማረሚያ ቤቶች በእስር ላይ ያሉ ሰዎች መብቶች ጥበቃ እና አያያዝ መሻሻል ማሳየታቸው እና ለአብዛኛዎቹ አቤቱታዎች አወንታዊ መፍትሔ እንዲያገኙ መደረጉን ኮሚሽኑ ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት ጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል በሪፖርት ዘመኑ ኮሚሽኑ በደረሱት አቤቱታዎችና በራሱ አነሳሽነት በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል፣ በአፋር፣ በሱማሌ፣ በአማራ እና ደቡብ ክልሎች በሚገኙ 59 የተፈናቃይ እና የስደተኞች መጠለያዎች፣ እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር የሚኖሩ ተፈናቃዮች እና የተመላሾች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ክትትል ማድረጉን ገልጿል፡፡
ከምርመራ ሥራ ጋር በተገናኘ ኮሚሽኑ በጋምቤላ ከተማ በነበረው ውጊያ የተነሳ በደረሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ ሪፖርት ይፋ ማውጣቱን፤ የሴቶች እና ሕፃናት መብቶች የሚመለከቱ የሕግ ማዕቀፍችእና በአተገባበር ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ለመለየት የሚያስችሉ ምርምር መደረጉን ለምክር ቤቱ በቀረበው የሪፖርት ማብራሪያ ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም በሕገ ወጥ እና በዘፈቀደ እስር ላይ ትኩረቱን ያደረገ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውበሕዝብ ፊት የሚካሄድ ግልጽ የምርመራመድረክ በሃዋሳ፣ በጂግጅጋ፣ በባሕር ዳር እና በአዳማ ከተማ ተዘጋጅቷል፡፡ በደቡብ ክልል በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅት እና በድኀረ ምርጫ በወረዳዎች እና ዞኖች የሰብአዊ መብት አያያዝን በተመለከተ ክትትል በማድረግ ሁለት ሪፖርቶች ተዘጋጅተዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ባለፉት ዘጠኝ ወራት “በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ግጭት በሰላም ለመቋጨት የተደርገው ስምምነት፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ እና በቤንሻንጉል ክልሎች ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው ጥረት፣ የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎችና ምክክሮች በጥሩ ጎኑ የሚነሱ ስራዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም “በአንጻሩ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴና የሰብአዊ መብቶች እንደምታው፣ የዘፈቀደ እስርና በእስር ወቅት የሚደርስ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ፣ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የጸጥታ ኃይሎች የሚወስዱት ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ፣ በጋዜጠኞች፣ በሚዲያ፣ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ተቃዋሚ ድምጾች ላይ ያነጣጠረ ጥቃትና የቅድመ ክስ እስር፣ ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ላይ የተጣሉ የዘፈቀደ ገደቦች፣ በድርቅ፣ ሕጋዊ ሂደትን ያልተከተለ የቤቶች ፈረሳ እና በግዳጅ ማስነሳት አሳሳቢ ጉዳዮች ሆነው ቀጥለዋል” ሲሉ አብራርተዋል።
በተመሳሳይ “በከፍተኛ የኑሮ ውድነት የተነሳ በሕዝብ ላይ የደረሰ እንግልትና የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ጥሰቶች፣ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን መልሶ በማቋቋም ገና ብዙ ሥራ የሚጠብቅ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ ሁሉ ችግሮች በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአካል ጉዳተኞችና በአረጋውያን ላይ ተደራራቢ ለሆኑ የመብት ጥሰቶች የሚያጋልጥ መሆኑን” ዋና ኮሚሽነሩ አስረድተዋል። በተጨማሪም “ኮሚሽኑ የፖሊስ ጣቢያዎችንና ሌሎች መደበኛ ያልሆኑ ሰዎች የታሰሩባቸውን ቦታዎች በቀላሉ ለመጎብኝት አለመቻሉና የበጀት አቅም ውስንነት አሳሳቢ ሆነው እንደቀጠሉ ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።