።
ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በባንክ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው የውጭ ባለሀብቶች አምስት የሚደርሱ የባንክ ፈቃድ ለመስጠት ማቀዷ ተገለጸ፡፡
የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሦስት እስከ አምስት ለሚደርሱ በኢትዮጵያ በባንክ ዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች የባንክ ፈቃድ እንደሚሰጥ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይህም የአገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ አገልግሎት ለውጭ ተፎካካሪዎች ክፍት ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡
እስካሁን የባንኩ ዘርፍ ለውጭ አገራት መዋዕለ ነዋይ አፍሳሾች ዝግ ሆኖ የቆየ ሲሆን፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ ግን ለውጭ አገራት ተፎካካሪዎች ክፍት እንደሚደረግ ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም የውጭ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ዘርፉም ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በጋራ የሚሰሩበት አማራጭ ሊኖር እንደሚችል በምክትል ገዥው በኩል ተጠቅሷል፡፡
የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለይም በባንክ፣ በቴሌኮም፣ በትራንስፖርት እና አቬሽን ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ካሳዩ ቆይተዋል ተብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለውጭ ኢንቨስተሮች ዝግ ተደርገው የቆዩ ዘርፎች ክፍ እንደሚደረጉ ቃል የገቡ ሲሆን፤ የመጀመሪያው የውጭ ቴሌኮም ፈቃድ ማግኘቱም ይታወቃል፡፡
በተጨማሪም የመንግሥት የልማት ድርጅት እና ብቸኛ የቴሌኮም ድርጅት ሆኖ የቆየውን የኢትዮ ቴሌኮም 45 በመቶ ድርሻ ለውጭ ባለሀብት በመሸጥ ሦስተኛ የውጭ ቴሌኮም ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ መጀመሩ ተገልጿል፡፡