በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ባለችው ሱዳን እስካሁን የተገደሉ ዜጎች ቁጥር ከ350 በላይ አሻቅቧል።
ይህ በዚህ እንዳለ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሱዳን ግዛት ገብቶ ወረራ ፈጽሟል የሚሉ ዜናዎች በበርካታ የሱዳን ሚዲያዎች ተዘህበዋል።
ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ ዛሬ ባወጣችው መግለጫ ምንም አይነት ወታደር ወደ ሱዳን ግዛት አለማስገባቷን አስታውቃለች።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ “በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ግጭት መቀስቀስ የሚፈልጉ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በመግለጫቸው አንዳንድ አካላት የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነትን ለማበላሸት በማሰብ፣ “ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ሱዳን ውስጥ አስገብታለች በማለት ሐሰተኛ መረጃ እያሠራጩ ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ውዝግብ ቢኖራቸውም ልዩነታቸው በንግግር ይፈታል ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያ አሁን ሱዳን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ለድንበር ውዝግቡ መጠቀሚያ ልታደርገው አትፈልግም” ሲሉም ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ተናግረዋል ።
ዐቢይ ወንድም የኾነው የሱዳን ሕዝብ እንዲህ ላሉት ሐሰተኛ ወሬዎች ጆሮ እንደማይሰጥ እምነታቸውን መኾኑንም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም፣ አንዳንድ ወገኖች ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ በነበረችበት ወቅት “ሉዓላዊነቷን በመጣስና መሬቷን በኃይል በመቆጣጠር የፈጸሙትን ድርጊት ኢትዮጵያ በሱዳን ላይ አትፈጽመም” ብለዋል።
ዐቢይ፣ የኢትዮጵያ ሱዳን ግንኙነትን ለማበላሸት ሲሉ “ሐሰተኛ መረጃ” እያሠራጩ ነው ያሏቸውን ማንነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን አልፋሽጋ በተሰኘው መሬት ጉዳይ ይገባኛል በሚል ግጭት ውስጥ የገቡ ሲሆን በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተቀሰቀሰበት ወቅት ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት ወራለች።