ለሁለት ሀገር በቀል ኩባንያዎች የከፍተኛ ደረጃ የደለል ወርቅ ምርት ፈቃድ ተሰጥቷል።
የማዕድን ሚኒስቴር ለሁለት ኩባንያዎች የከፍተኛ ደረጃ የደለል ወርቅ የማምረት ፈቃድ መስጠቱን ገልጿል።
ፈቃድ የተሰጣቸው ቤአኤካ ጠቅላላ ንግድ ሥራ እና ኢልኔት ቴክኖሎጂ ግሩፕ የተሰኙት ሀገር በቀል ኩባንያዎች ናቸው።
“ቤአኤካ” ፈቃድ የተሰጠው በጋምቤላ ብሄራዊ ክልል ማጃንግ ዞን፣ ማንግሽ ወረዳ ሲሆን ለፕሮጀክቱ ከ138 ሚሊየን ብር በላይ መመደቡ ተገልጿል፡፡
ይህ ኩባንያ በሚቀጥሉት 4 ዓመታት ውስጥ 911 ሺህ ኪሎ ግራም ወርቅ ያመርታል ተብሏል።
ሌላኛው ፈቃድ የተሰጠው ተቋም “ኢልኔት ቴክኖሎጂ ግሩፕ” ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ አሶሳ ዞን፣ አሶሳ እና ሁዱሉ ወረዳዎች እንደሆነ ተገልጿል።
ይህ ኩባንያ ለፕሮጀክቱ ከ148 ሚሊየን ብር በላይ መመደቡ አስታውቋል፡፡
የፈቃዱ የአገልግሎት ዘመን ለአስር ዓመታት የሚቆይ ሲሆን በሶስት ወራት ውስጥ የፋብሪካ ግንባታውን ጨርሶ ወደ ምርት ይገባል ተብሏል።
ኩባንውያ በሚቀጥሉት 4 ዓመታት ውስጥ 440 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማምረት ተስማምቷል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከወርቅ ንግድ የሚገኘው ገቢ እየጨመረ ቢሆንም በዚህ ዓመት ግን ገቢው በህገወጥ ንግድ ምክንያት ማሽቆልቆሉን ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ከሁለት ሳምንት በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።