ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ እን አይኤምኤፍ ጋር ስታደርገው የነበረው ውይይት ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ የፋይናንስ ልዑክ ከዓለም ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘባ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ሃላፊዎች ጋር በዋሽንግተን ለአንድ ሳምንት ሲያደርግ የነበረውን ውይይት አጠናቅቋል፡፡
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሽ በቀለ በትዊተር ገጻቸው እንዳስታወቁት በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና በብሄራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የተመራው ልዑክ ከዓለም ባንክ እና ከዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ዳይሬክተሮች ጋር ሲያደርግ የነበረው ውይይት ተጠናቋል፡፡
የፋይናንስ ልዑኩ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂየቫ እና ልዑካቸው ጋር ምክክር ማድረጋቸውን እና ለአንድ ሳምንት የቆየውን ውይይት መጠናቀቁን አንስተዋል፡፡
የተደረገው ውይይት ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትን የልማትና ሰብዓዊ ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ይሁንና ኢትዮጵያ ከፋይናንስ ተቋሙ ምን ያህል ገንዘብ እንደምታገኝ እስካሁን አልተጠቀሰም።
አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ ብድር ከሚፈቅዱ ሀገራት መካከል ዋነኛው ሲሆን የሀገር በቀል ኢኮኖሚ እቅድን ለመደገፍ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ብድር እንደሚፈቅድ ይጠበቃል።