የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን እያወጣች ነው።
መግለጫዎቹ ኢትዮጵያ በቀጣይ ክረምት ወራት ግድቡ ውሀ እንዲይዝ የተናጠል ውሳኔ እንዳትወስን የሚያሳስቡ ናቸው።
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ከጋዜጠኞች ለቀረበው ጥያቄ “ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ውሀ አሞላል ዙሪያ ማንንም የማስፈቀድ ግዴታ የለባትም” ብለዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ግዛት እና ሀብት እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት ነው የሚሉት አምባሳደር መለስ በእቅዳችን እና በፕሮግራማችን እንመራለን ሲሉም አክለዋል።
የግብጽ ሰሞንኛ ተደጋጋሚ መግለጫ የህዳሴው ግድብ አራተኛ ዙር ውሀ መመሙያ ጊዜ እየተቃረበ መምጣቱን ተከትሎ ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ ያለመ እንደሆነም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል ።
አምባሳደር መለስ በዛሬው መግለጫቸው ላይ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከልም ሌላኛው ጉዳይ በፌደራል መንግስት እና ህወሀት መካከል በደቡብ አፍሪካ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ነው።
የስምምነቱን አተገባበር የሚከታተለው አፍሪካ ህብረት ያቋቋመው የስምምነቱ ክትትል እና ማረጋገጫ ቡድን የተጠቃለለ ሪፖርቱን በቀጣይ ይፋ ያደርጋል ተብሏል።
ይህ የባለሙያዎች ቡድን የስምምነት አተገባበር ሪፖርቱን ገና እንዳላጠናቀቀ የገለጹት ቃል አቀባዩ በቀጣይ ይፋ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።
የጣልያን ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂያ ሜሎኒ የፊታችን አርብ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው የጠቅላይ ሚንስትር ሜሎኒ ጉብኝት ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ይወያያሉም ተብሏል።