በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን የመጡበትን ቀን በድጋፍ ሰልፍ ሲያከብሩ በአማራ ክልል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን የመጡባትን ቀን መከራ እና ሞት እንጂ ለውጥ አላመጣልንም ሲሉ በሰላማዊ ሰልፍ ላይ ገልጸዋል፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት በህወሃት የበላይነት ይመራ የነበረው ኢህአዴግ ህዝባዊ ተቃውሞ መበርታቱን ተከትሎ ነበር የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሀይለማርያም ደሳለኝ መጋቢት 2010 ዓ.ም ስልጣን የለቀቁት፡፡
ይህን ተከትሎም አብይ አህመድ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝን ተክተው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም ሹመቱን በተቀበሉበት ወቅት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃለ መሀላ ሲፈጽሙ የበርካቶችን ድጋፍ እና አድናቆት ያገኙ ቢሆንም በሁለት ዓመት ውስጥ ግን ድጋፋቸው አሽቆልቁሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም በየቦታው ዜጎች ማንነታቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ መገደላቸው፣ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት መገደብ፣ ያልተገባ እስር እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ማስቆም አልቻሉም በሚል ትችቶችን አስተናግደዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በጎረቤት ሀገራት ሲጣስ ዝም ማለት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆን እና ለወጡበት ማህበረሰብ አድሏዊ አሰራሮችን ፈጽመዋል በሚልም እየተተቹ ይገኛሉ፡፡
ይሁንና ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን የመጡበት ቀንን አስመልክቶ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የጠካሄደው ሰልፍ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ ለመስጠት ሲሆን በአማራ ክልል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና መንግስታቸውን ለመተቸት ያለመ እንደሆነ ሰልፈኞቹ ወደ አደባባይ ይዘዋቸው የወጧቸው መልዕክቶች ያስረዳሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ መንግስታቸው እስካሁን ባለፉት አምስት ዓመት ቆይታ ስለነበራቸው ስራዎች ያሉት ነገር የለም፡፡