ኢትዮጵያ ወደ አግዋ የመመለስ እድል አላት?

በሰሜን ኢትዮጵያ በፌደራል መንግሥት እና ህወሀት መካከል ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ ነበር አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአሜሪካ የንግድ ችሮታ (አግዋ) እድል ያገደችው።

የእግዱ ዋነኛ ምክንያትም በጦርነቱ ምክንያት በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው የሚል ሲሆን ኢትዮጵያ የአሜሪካንን ውሳኔ ተቃውማም ነበር።

የአግዋ እድል መሰረዝ በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ባሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የተቀጠሩ ዜጎችን ስራ አጥ በማድረግ በጦርነቱ ምንም አይነት ተሳትፎ የሌላቸው ኢትዮጵያዊያንን ይጎዳል ስትል ኢትዮጵያ አሜሪካ ውሳኔዋን እንድታጤነው ጠይቃም ነበር።

ይሁንና ዋሸንግተን ኢትዮጵያን ከአግዋ እግድ እስካሁን ያላነሳች ሲሆን የመነሳት እድል ይኖራት ይሆን የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

ጥያቄው በተለይም የጦርነቱ ዋነኛ ተሳታፊዎች የሆኑት የፌደራል መንግሥት እና ህወሀት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ጥያቄው እያየለ መጥቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በሳምንታዊ መግለጫቸው ላይ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን በቆይታቸው ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር እና ሌሎች ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት በአሜሪካ እገዳ የተጣለባት አግዋ እድል እንድትመለስ ለዋሸንግተን በይፋ ጥያቄ አቅርባለች? በሚል በመግለጫው ላይ የነበሩ ጋዜጠኞች ለቃል አቀባዩ አቅርበዋል።

አምባሳደር መለስ ዓለምም “አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ የጣለችውን የአግዋ እድል እንድታነሳ ጥያቄው ከቀረበ መቆየቱን ነገር ግን አሁንም እግዱ እንዳልተነሳ ጉዳዩ ተጨማሪ ምክክር እና ውይይት ይፈልጋል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከንም “የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ትግበራ በስምምነቱ መሰረት ከተፈጸመ ኢትዮጵያ ወደ አግዋ እድል ልትመለስ ትችላለች” ብለዋል።

የአሜሪካ ንግድ ችሮታ ወይም አግዋ በፈረንጆቹ 2000 ላይ የአፍሪካ ሀገራት ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ ገበያዎች ከቀረጥ ነጻ በሆነ መንገድ እንዲያቀርቡ የሚፈቅድ እድል ሲሆን በየ25 ዓመቱ የሚታደስ ነው።

አሜሪካ ይህን እድል የዲሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ያለቻቸውን ሀገራት ከእድሉ ታግዳለች።

ኢትዮጵያ ፣ማሊ እና ጊኒ የአግዋ እድል መስፈርቶችን አያሟሉም በሚል በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትዕዛዝ ከእድሉ የተሰረዙ ሀገራት ናቸው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *