24
Apr
ኢትዮጵያ 50 ሺህ ኩንታል ስንዴ ለሱዳን ለመላክ መዘጋጀቷን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ በ”ኢትዮጵያ ኤይድ” በኩል የሚቀርበው ድጋፍ በርካታ መድሃኒቶችንም እንደሚያካትት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል ። ለሱዳን ህዝብ በአሁኑ ወቅት የሚያስፈልገውን ድጋፍ ከማቅረብ ባሻገር ተፋላሚዎቹን ወገኖች ለመሸምገልም ኢትዮጵያ ፍላጎት እንዳላት አንስተዋል። ለሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አልቡርሃን እና ለፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አርኤስኤፍ) አዛዡ ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎም በድጋሚ ለንግግር ቦታ እንዲሰጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰሜኑ ጦርነት በድርድር እንዲቆም ላደረጉ አካላት እውቅና ሲሰጡ ነው ጥሪውን ያቀረቡት። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው የኦሮሚያ ነጻ አውጭ ሰራዊት ጋር ድርድር እንደሚደረግ ተናግረዋል ። ድርድሩ በታንዛኒያ የሚካሄድ ሲሆን ኖርዌይ እና ኬንያ አደራዳሪዎች ይሆናሉ ተብሏል።