የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሠራተኛ የመቀነስ ዕቅድ እንደሌለው ገለጸ

የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ ለመንግስታዊው የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ጋዜጣ ፕላስ ክፍል በሰጡት ቃል “በኢትዮጵያ ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ክፍት የመንግሥት የሥራ መደቦች ባሉበት ሁኔታ ምንም ዓይነት ሠራተኞችን የመቀነስ ዕቅድ የለም ” ሲሉ ገልጸዋል።

በፌዴራልና በክልል ደረጃ የመንግሥት የሥራ መደቦችን የመረጃ የማጥራትና የማደራጀት ሥራ በተግባር መከናወኑንና ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሥራ መደቦች መኖራቸው መለየቱን ገልጸዋል።

ከእነዚህ ወደ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚጠጉት  በሠራተኞች የተያዙ ሲሆን፤ ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ከፍት የሥራ መደቦች ይገኛሉ ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የስራ መደቦችን የማጠፍ ዓላማ እንዳልተያዘም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ ካላት እያደገ ከመጣ የሕዝብ ብዛትና የአገልግሎት ፍላጎት አንጻር ተጨማሪ የመንግሥት ሠራተኞች ያስፈልጓታል ” ያሉት ኮሚሽነሩ “በአሁኑ ወቅት እየተተገበረ ያለው አጠቃላይ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ዋና ዓላማ ሠራተኞችን መቀነስ ሳይሆን፣ በተመደቡበት የሥራ ዘርፍ ብቃታቸውን፣ ክህሎታቸውንና አገልግሎት የመስጠት አፈጻጸማቸውን ማሳደግ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“አዲሱ የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የመንግሥት ሠራተኞች ይቀነሳሉ የሚሉ የተሳሳቱ መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲሰራጩ ነበር እነዚህ ወሬዎች የሪፎርሙን አገራዊ ዓላማና ተቋማዊ ይዘት በትክክል የማያሳዩ ናቸው” ሲሉ ውድቅ አድርገዋል።

“የሪፎርሙ ዋና ዓላማ ሠራተኞች በተመደቡበት የሥራ መደብ ላይ በከፍተኛ ብቃትና ኃላፊነት መስራት መቻላቸውን ማረጋገጥ ፤ በሥራቸው የሚጠበቀውን ብቃትና አፈጻጸም የማያሳዩ ሠራተኞች ካሉ ቦታውን በብቃት ሊሠሩ በሚችሉ ሌሎች ባለሙያዎች የመተካት እንጂ የሥራ መደቦችን የማጠፍና ሠራተኞች የመቀነስ ዓላማ የለውም ” ሲሉ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ሰራተኞቹን ከአንድ ዓመት በፊት ፈተና በመፈተን አዲስ ምደባ የሰጠ ሲሆን ሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ መንገድ ለመከተል የትምህርት ማስረጃዎችን በማጣራት ላይ ናቸው።

የፌደራል ተቋማትም የሙያ ምዘና ፈተናዎችን በመስጠት ላይ ሲሆኑ የሰራተኞቹ ፈተና ውጤቶችን መሰረት በማድረግ የደረጃ እድገት እና ስራ ምደባ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *