አሜሪካ ባወጣችው አዲስ መግለጫ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ተቋማት ላይ የረጅም ርቀት ጥቃቶች ሊሰነዘሩ እንደሚችል አስጠንቅቋል።
አሜሪካ በአዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል ባወጣችው መግለጫ በጥቅምት ወር በኢትዮጵያ ወታደራዊ ተቋማት ላይ የረጅም ርቀት ጥቃቶች ሊሰነዘሩ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ዘገባዎች እንደደረሷት ገልጻለች።
አሜሪካ አክላም ዜጎቿ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉና ባለሥልጣናት የሚሰጡትን መመሪያ እንዲከተሉ አሳስባለች።
አሜሪካ ማምሻውን ባወጣችው የደህንነት ማስጠንቀቂያ በተጨማሪም ዜጎቿ በማንኛውም ምክንያት ወደ አማራ ክልል ላሊበላን ጨምሮ፣ ወደ ትግራይ ክልል ወይም ወደ ዓፋር ክልል ከማንኛውም ዓይነት ጉዞ እንዲቆጠቡ አሳስባለች።
ቀደም ሲል በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎቿ ደህንነታቸው የተጠበቀ ከሆነ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ፣ ካልሆነ ደግሞ ሁኔታዎች እስኪሻሻሉ ድረስ ባሉበት ቦታ እንዲጠለሉ አሳስባለች።
የአሜሪካ ዜጎች ራሳቸውን ከጥቃት እንዲጠብቁ ትኩረት ያደረገው ይህ መግለጫ ይህ የረጅም ርቀጥ ጥቃት ከማን ሊሰነዘር እንደሚችል ያለው ነገር የለም።
በኢትዮጵያ ያለው የደህንነት ስጋት ከፍ ማለቱን በርካታ ሀገራት እየገለጹ ሲሆን ክስተቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ካለው ግጭት ጋር የተያያዘ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ እና ዙሪያው ባሉ አካባቢዎች ድሮን ማብረርን መከልከሉ ይታወሳል።
ሮይተርስ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በአዲስ አበባ ፍንዳታዎች መከሰታቸውን የዘገቡ ቢሆንም ከኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ሌሊት ላይ ተሰማ ስለተባሉት ፍንዳታዎችም ሆነ ጉዳት ስለመድረሳቸው የተገለጸ ነገር የለም።
ህጋዊ እውቅናው በምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ህወሀት እና ሌሎች በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀስ አማጺ ቡድኖች ስልጣን በሀይል ለመቆጣጠር በማለም ህብረት መፍጠራቸውን ካሳወቁበት ጊዜ ጀምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ስጋት ጨምሯል።
አማጺ ቡድኖችን እንደሚደግፍ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ክስ የሚቀርብበት የኤርትራ መንግሥት በትግራይ ክልል በኩል የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ጥሶ መግባቱ ተገልጿል።
የመንግስት ኮሙንኬሽን ሚንስትሯ እናታለም መለሰ ለብሉምበርግ እንዳሉት የኤርትራ ጦር ባስቸኳይ የኢትዮጵያን ግዛት ለቆ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
አሜሪካንን ጨምሮ ብሪታንያ፣ የአውሮፓ ህብረት ፣ የአፍሪካ ህብረት እና ተመድ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደከፋ ግጭት እንዳያመሩ ጥሪ አቅርበዋል።