ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመሩ የቆዩት አብይ አህመድ (ዶ/ር) ለተጨማሪ አምስት ዓመታት በስልጣናቸው ላይ እንዲቆዩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርጠዋል፡፡
54 ሚሊዮን መራጮች የተሳተፉበት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫን ተከትሎ ብልጽግና ፓርቲ 438 የፓርላማ ወንበሮችን በመቆጣጠር በአብላጫ ድምጽ ማሸነፉን ተከትሎ አዲሱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመስርቷል፡፡
በፌደራል መንግስት “ከፍተኛ የአስፈጻሚነት ስልጣን” ያለው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመረጠው፤ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል እንደሆነ በስራ ላይ ያለው የኢፌዲሪ ህገ መንግስት ይደነግጋል።
በዚህ መሰረት ገዢው ፓርቲ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት በድጋሚ በዕጩነት ያቀረበው፤ በጅማ ዞን ጎማ 2 የምርጫ ክልል ለፓርላማ የተመረጡትን አብይ አህመድን ነው።
አብይ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመረጡት፤ ለአምስት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ይዘው የነበሩትን አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን በመተካት ነው።
በመሪነት መንበር ላይ ለሶስት ዓመት ከመንፈቅ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ከስድስተኛው ዙር ምርጫ በኋላ በመስከረም 2014 ዓ.ም. በተካሄደው የመንግስት ምስረታ በድጋሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተመርጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ አዲሱን የካቢኔ አባላት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው እንደሚያጸድቁ ይጠበቃል፡፡ ይህ በዚህ እንዳለም ከ10 ዓመት በላይ በሚንስትርነት ያገለገሉት አቶ አህመድ ሽዴ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ሆነው ተሾመዋል፡፡
ከቀድሞው የሀገሪቱ ስርዓት ኢህአዴግ ጀምሮ በመንግስት ከፍተኛ ሹመት ውስጥ የቆዩት አቶ አህመድ ሽዴ አዲሱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ተሾመዋል።
ባሳለፍነው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው ሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ውጤትን ተከትሎ በመጭዎቹ አምስት ዓመታት የሀገሪቱን ህግ ማውጣት እና ትርጉም የመስጠት ስርዓቱን የሚመሩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ፌዴሬሽን ምክር ቤት በይፋ ተመስርተዋል።
ይህን ተከትሎም ባለፉት ስምንት ዓመታት የገንዘብ ሚንስትር የነበሩት አቶ አህመድ ሽዴ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ሆነው ሲሾሙ የስራ እና ክህሎት ሚንስትር የነበሩት ሙፈሪያት ካሚል ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ተሾመዋል።