የአፍሪካ ቁጥር አንድ ቢሊኒየር ናይጀሪያዊው አሊኮ ዳንጎቴ በኬንያ ላሙ አካባቢ ለመገንባት ላቀዱትና በቀን 700,000 በርመል ነዳጅ የማጣራት አቅም የሚኖረው ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ማቀዱ ይታወሳል።
ይህ ፕሮጀክት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የ30 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ እንዲገዙ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን ኢትዮጵያ የተወሰነ ድርሻ የመግዛት ፍላጎት እንዳላት ተገልጿል።
የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ የኢኮኖሚ አማካሪ ዴቪድ ንዲ በናይሮቢ በተካሄደ የካፒታል ማርኬት መድረክ ላይ ይህንን የኢትዮጵያ ፍላጎት ይፋ ማድረጋቸውን እንደሆነ ብሉምበርግ ዘግቧል።
አማካሪው ከዚህ ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የ30 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ መቅረቡን ገልጸዋል።
አማካሪው አክለውም፥ ኬንያ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣውን የ10 በመቶ ድርሻ ለመግዛት ፍላጎት ማሳየቷንና ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳም በፕሮጀክቱ ላይ የባለቤትነት ድርሻ ለመግዛት ፍላጎት ማሳየታቸውን በመድረኩ ላይ ተናግረዋል።
እስከ 16 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይደረግበታል ተብሎ የሚገመተው ይህ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ፣ አጠቃላይ ወጪው 20 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል።
የነዳጅ ማጣሪያው ግንባታ መሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ መርሐግብሩ መስከረም ወር ላይ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በኩል በጎረቤት ሀገራት ዋና ዋና መሰረተ ልማት ላይ አክስዮኖችን የመግዛት ፍላጎት በማሳየት ላይ ትገኛለች።
ለአብነትም በራስገዟ ሶማሊላንድ ንብረት በሆነው በርበራ ወደብ የ19 በመቶ ድርሻ፣ በደቡብ ሱዳን የባንክ፣ ቴሌኮም እና ሪልኢስቴት ኢንቨስትመንት ተሰማርታለች።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶችን ከፊል ባለቤትነት ያለው ሲሆን ለአብነትም በዛምቢያ፣ ማላዊ፣ ምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ይጠቀሳሉ።
ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ ከካሜሩን፣ ጅቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት በጋራ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ፈጽሟል።
ቢሊየነሩ አሊኮ ዳንጎቴ በኢትዮጵያ ቢሊዮን ዶላሮችን ኢንቨስት ያደረገ ሲሆን በሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ነዳጅ ማጣሪያ እና የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካዎችን በመገንባት ላይ ይገኛል።