የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ ኤርፖርትን ለመገንባት ከስምንት በላይ ሀገራት እየተፎካከሩ ነው ተባለ

ኢትዮጵያ የቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት መንገደኞችን ከማስተናገድ አንጻር እቅሙ ተዳክሟል በሚል ምክንያት በ12 ቢሊዮን ዶላር አዲስ ኤርፖርት ለመገንባት ማቀዷ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም ቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በ12 ቢሊዮን ዶላር ለመገንባት የዲዛይን ስራው ተጠናቆ የተቋራጭ ድርጅቶች መረጣ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በዚህ ኤርፖርት ግንባታ የመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ዓለም አቀፍ ተቋራጮች እንዲወዳደሩ ዓለም አቀፍ የመጀመሪያ ዙሪ ማስታወቂያ መውጣቱን ተከትሎ የአሜሪካ ፣ አውሮፓ ፣ እስያ እና ሌሎችም ሀገራት ፍላጎታቸውን አሳውቀዋል።

በዚህም መሰረት የቻይና የግንባታ ተቋማት በብዛት ፍላጎታቸውን እንዳሳዩ ተገልጿል።

በቀረበው የእጩዎች ዝርዝር መሰረት ከወጡት አራት ዋና ዋና የሥራ ክፍሎች  ውስጥ የቻይና ተቋማት በተናጠልና በቅይጥ በብዛት ተካተዋል።

የቻይና ኮሙኒኬሽንስ ኮንስትራክሽን ኩባንያ (CCCC)፣​ቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን (CCECC) እና  ቤጂንግ አርባን ኮንስትራክሽን ግሩፕ (BUCG) ይገኙበታል።

​ከቻይና በተጨማሪ ከቱርክ አይሲ ኢክታስ  እና ካልዮን ከጣሊያን Webuild፣ ከፈረንሳይ VINCI፣ ከኳታር፣ ከደቡብ ኮሪያ ሳምሰንግ ሲ ኤንድ ቲ ፣ ከህንድ፣ ከሩሲያ እንዲሁም ከፖርቱጋል የተወጣጡ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በጽኑ ውድድር ውስጥ ይገኛሉ።

የአሜሪካው ሌን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን  በቅይጥ አጋርነት በመካተት አዲሱን ኤርፖርት ለመገንባት ፍላጎት ካሳዩ ተቋራጮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።

​ፕሮጀክቱ ዋናውን ተርሚናል፣ የአየር መንገድ መሰረተ ልማቶችን፣ ደጋፊ ህንፃዎችን እና የትራንስፖርት መስመሮችን የሚያካትት ሲሆን፣ የመጨረሻዎቹን አሸናፊዎች የመለየት ሂደት እስከ ጥር 2019 ዓ.ም ተራዝሟል።

የጨረታ ማስታወቂያው የተራዘመው ተወዳዳሪዎች የቴክኒክ እና የፋይናንስ ፕሮፖዛሎቻቸውን በበቂ ሁኔታ እንዲያዘጋጁ ተጨማሪ ጊዜ ለመስጠት ታስቦ መሆኑ ተገልጿል።

​በሌላ በኩል፣ ዋሽንግተን የቦይንግ አውሮፕላኖች ግዥን ከፕሮጀክቱ ጋር በማያያዝ የአሜሪካ ኩባንያዎች በግንባታውና በፋይናንስ አቅርቦቱ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች ተብሏል።

የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም የሚኖረው ሲሆን፣ በአፍሪካ ግዙፉ የአቪዬሽን ፕሮጀክት እንደሆነ ይታመናል። 

የቻይና እና ጣልያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ሜጋ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት ጥሩ ታሪክ ያላቸው ሲሆን በተለይም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ ሌሎች የሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን የጣልያኑ ኩባንያዎች በስኬት አጠናቀዋል።

የቱርክ ኩባንያዎችም በአዋሽ ኮምቦልቻ-ወልደያ ባቡር መስመር ግንባታ ላይ የተሳተፉ ቢሆንም ይህ ፕሮጀክት ውጤታማ ሳይሆን ቀርቶ ጉዳዩ በዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት ላይ እየታየ ነው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *