የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት እና አንጋፋ ዲፕሎማት የሆኑት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዲስ ሹመት ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡
ሹመቱን የተመድ ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ እንደሰጡ ቢሮው በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ ላይ ጠቅሷል።
ፕሬዝደንቷ የተመደቡት በምእራብ አፍሪካና ሳህል ቢሮ ውስጥ ገለልተኛ ስትራቴጂያዊ ግምገማ እንዲያደርጉ ሲሆን፣ ዋና ተግባራቸውም ተቋሙ ለአካባቢው ቀውሶች በሚሰጠው ዘገምተኛ ምላሽ ሳቢያ የሚነሱበትን ትችቶችና የአሰራር ክፍተቶችን መመርመር ነው።
ወይዘሮ ሳህለወርቅ ከሀምሌ ወር ጀምሮ አዲሱን ሹመት ተቀብለው ስራ እንደሚጀምሩ ተገልጿል፡፡
ወይዘሮ ሳህለወርቅ ስራቸውን ከመጀመራቸው በፊት በመጀመሪያ ወደ ኒውዮርክ በማቅናት ከፀጥታው ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ይቀበላሉ የተባለ ሲሆን፣ በመቀጠልም የተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ወደሚገኝበት ሴኔጋል ዳካር በመጓዝ ከከፍተኛ አመራሮች ጋር ይወያያሉ።
ለቀድሞዋ ፕሬዝደንት ይህ ታላቅ ኃላፊነት ሊሰጣቸው የቻለው ቀደም ሲል በሴኔጋል፣ ማሊ፣ ጊኒና ኬፕ ቨርዲ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ባገለገሉበት ወቅት ስለ ቀጠናው ባላቸው እውቀት እና ልምድ አማካኝነት ነው ተብሏል፡፡
የ76 ዓመቷ የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢትዮጵያ አምስተኛ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተሾሙ አምስተኛ ዓመታቸውን አጠናቀው ከሁለት ዓመት በፊት በአምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ መታካታቸው ይታወሳል፡፡
በፈረንሳይ ሞንትፕሌር ዩንቨርሲቲ የተማሩት አንጋፋዋ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ከፕሬዝዳንትነት ሀላፊነታቸውን ከለቀቁ በኋላ በእረፍት ላይ ነበሩ፡፡
በዲፕሎማትነት ከ36 ዓመት በላይ ያገለገሉት ዲፕሎማቷ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አፍሪካ ህብረት፣ ፈረንሳይ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዝያ እና ሌሎችም ሀገራት በዲፕሎማትነት አገልግለዋል፡፡