በኢትዮጵያ ላይ ተጥሎ የነበረው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ መነሳቱን አሜሪካ አስታውቃለች።
ማዕቀቡ መነሳቱን የገለፀው በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአገር መከላከያ ንግድ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ነው።
ዳይሬክቶሬቱ፣ በኢትዮጵያ ላይ ይከተል የነበረውን የክልከላ ፖሊሲ በማንሳት አሁን ላይ በዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያ ዝውውር ደንብ (ITAR) ቁጥጥር የሚደረግባቸውን እና ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዙ የፈቃድ ማመልከቻዎችን በየተራ እየገመገመ ነው።
ይህን ተከትሎ በቅርቡ በሚወጣ የደንብ ለውጥ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የጦር መሳሪያ ዝውውር ደንብ – ITAR 126.1 ዝርዝር ውስጥ ከሚገኙ አገራት ተርታ “እንድትሰረዝ” የሚደረግ መሆኑን ጠቅሷል።
ይህ ደንብ በአሜሪካ ማዕቀብ ስር የሚገኙ የተወሰኑ አገራት፤ ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለፖሊስ፣ ለደህንነት እና ለሌሎችም የአገር ውስጥ የጸጥታ ኃይሎቻቸው የሚሆኑ የመከላከያ ቁሳቁሶችን እና አገልግሎቶችን ከውጭ ገዝተው ማስገባትም ሆነ ወደ ውጭ አገራት መላክ እንዳይችሉ የሚከለክል ነው።
ኢትዮጵያ በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ከነበረው የትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ እ.ኤ.አ ከኅዳር 2022 ጀምሮ ከ4 ዓመታት በላይ በዚህ ማዕቀብ ውስጥ ቆይታለች።
አሜሪካ ይህንን ማዕቀብ የጣለችው በወቅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ባጋጠመው ጦርነት ምክንያት የዜጎች ሰብዓዊ መብት ተጥሷል በሚል ነው።
ከጦር መሳሪያ ማዕቀቡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቀጠሉ እና አሜሪካ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ብሔራዊ ጥቅም ይጎዳል በሚል የኢኮኖሚ ማዕቀቦች የተጣሉ ሲሆን እስካሁን እነዚህ ማዕቀቦች አልተነሱም።
በተጣሉት ማዕቀብ ምክንያት በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተሰማርተው የነበሩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ኢትዮጵያን በመልቀቃቸው የኢኮኖሚ ጉዳት አድርሰዋል።