ለህክምና ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱ ሰዎች እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እንዲያሲዙ የሚያስገድድ መመሪያ ተዘጋጀ

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ወደ ውጭ አገር ሄደው ለሚታከሙ ዜጎች ጥራት ያለው፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ክብራቸውን የሚመጥን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ያለውን “የውጭ አገር የሕክምና አገልግሎት ቅብብሎሽ ሥርዓት ማስፈፀሚያ መመሪያ ቁጥር 1128/2018” አውጥቷል።

ይህ አዲስ መመሪያ በዋነኝነት የታካሚዎችን እንግልት ለመቀነስ፣ የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶችን ለመሙላት እና በሕክምና ስም የሚከናወኑ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር ታስቦ የተዘጋጀ  መሆኑን አስታውቋል።

መመሪያው በጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1362/2017 መሰረት የወጣ ሲሆን፣ ከሕክምና ቦርድ አሰራር ጀምሮ እስከ ወኪል ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ ድረስ ያሉ ሂደቶችን በዝርዝር ይደነግጋል።

በመመሪያው መሰረት አንድ ታካሚ ወደ ውጭ አገር ሄዶ እንዲታከም የሚፈቀድለት አራት ዋና ዋና መስፈርቶችን ሲሟሉ እንደሆነ ያስገድዳል።

ከመስፈርቶች መካከልም የሚፈለገው የሕክምና ዓይነት በሀገር ውስጥ የማይሰጥ መሆኑ መረጋገጥ አለበት ተብሏል።

እንዲሁም ለምርመራ የናሙና ዝውውር የማይቻል መሆኑን ማረጋገጥ፣ በከፍተኛ ወረፋ ምክንያት የታካሚው ሕይወት አደጋ ላይ የሚወድቅ መሆኑ ከተረጋገጠ እና ለክትትል የሚሄድ መሆኑን በሚመለከተው አካል ወይም በሕክምና ቦርድ ሲረጋገጥ ብቻ  እንደሆነ ይገልጿል።

ይህን ውሳኔ የሚሰጠው የሕክምና ቦርድ በሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር የሚመራና ከ3 እስከ 5 አባላት ያሉት ሆኖ በየሳምንቱ እየተሰበሰበ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ በመመሪያው  ላይ ተጠቅሷል።

ወደ ውጭ አገር ለመሄድ ፈቃድ የሚጠይቅ ታካሚ የጸደቀ የቦርድ ማስረጃ፣ የታደሰ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ማቅረብም ይኖርበታል ተብሏል።

በተጨማሪም ለሕክምናው የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን በባንክ ሂሳቡ ቢያንስ 500,000 ብር፣ ለንቅለ ተከላ (Transplant) ሕክምና ከሆነ ደግሞ 1,000,000 (አንድ ሚሊዮን) ብር መኖሩን የሚያረጋግጥ ሰነድ ማቅረብ እንዳለበትም መመሪያው ያስገድዳል።

ለንቅለ ተከላ ሕክምና የሚሄዱ ታካሚዎች ከለጋሹ ጋር ያላቸውን ስምምነትና የለጋሹን የጤና ሁኔታ የሚያሳዩ ተጨማሪ ሰነዶችን ማቅረብ ይኖርባቸዋል።

ታካሚዎችን ከውጭ አገር የሕክምና ተቋማት ጋር የሚያገናኙ ወኪሎች የጤና ባለሙያ መሆን እንዳለባቸውና ከሚኒስቴሩ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ማግኘት እንዳለባቸው ተደንግጓል።

ወኪሎች ለታካሚው ስለሚሰጠው አገልግሎት የተጋነነ መረጃ መስጠት የተከለከለ ሲሆን፣ በየ ሶስት ወሩ ለሚኒስቴሩ የስራ አፈፃፀም ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

ውጭ አገር የሚገኘው የጤና ተቋም ለሚሰጠዉ የህክምና አገልግሎት ለሚከሰት ጥራት ደረጃ ጉድለት፤ የህክምና ስህተት፣ የሙያ ግድፈት እና መሰል ድርጊቶች ለታካሚው ካሳ መክፈል እንዳለበት ተደንግጓል።

ካሳ የሚከፍለው “ተቋሙ” ቢሆንም፣ ወኪሉ ይህ ተጠያቂነት ያለበትን ተቋም የመምረጥና ጉዳዩን የማስፈጸም “ኃላፊነት” ይኖርበታል።

መመሪያውን በሚጥሱ ወኪሎች ላይ ሚኒስቴሩ እንደ ጥፋቱ ክብደት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ የብቃት ማረጋገጫን ማገድና እስከ መሰረዝ የሚደርስ እርምጃ  እንዲወስድ ይፈቅዳል።

በተለይም ሀሰተኛ ማስረጃ ማቅረብ፣ የታካሚውን ደህንነት አደጋ ላይ መጣልና ከሚኒስቴሩ እውቅና ውጭ መንቀሳቀስ ለብቃት ማረጋገጫ መሰረዝ ዋና ምክንያቶች ናቸው

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *