በጋሞ ዞን ባጋጠመ የመሬት መንሸራተት አደጋ የሟቾች ቁጥር 107 መድረሱ ተገለጸ

‎በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ፣ካምባ እና ቦንኬ በተባሉ ወረዳዎች በደረሰው የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋ የሟቾች ቁጥር 107 መድረሱን የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምሴ አድማሱ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

‎ከሟቾቹ መካከል ከጋጮ ባባ ወረዳ ብቻ 102፣ ከካምባ ወረዳ 2 እንዲሁም ከቦንኬ ወረዳ 3 በድምሩ የ107 ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

አስተዳዳሪው አክለውም እስካሁን በተከናወነው አስቸጋሪ ፍለጋ የ57 ሰዎች አስክሬን መገኘቱንና በጋጮ ባባ ወረዳ የቀሪ 50 ሰዎች አስክሬን እየተፈለገ መሆኑን ተናግረዋል።

‎የአከባቢው መልካምድር አስቸጋሪ መሆን አስክሬን ፍለጋውን ከባድ ማድረጉን የገለፁት የዞኑ አስተዳዳሪው ጉዳት ለደረሰባቸውና ለተፈናቀሉ ወገኖች አስቸኳይ የዕለት እርዳት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

‎የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት በበኩሉ የአደጋ መከታተያ ማዕከል፣ በተለይም ከመሬት ናዳና እና መሽራተት ጋር ተያይዘው አደጋ ሊከሰትባቸው የሚችሉ አካባቢዎችን በሳይንሳዊ ጥናት በመለየት ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቀድሞ ማሳወቁን አስታውቋል።

ይህን እንጂ መሰል የተፈጥሮ  አደጋዎችን ለመከላከልና የጉዳት መጠኑን ለመቀነስ የጥናቱን ውጤቶች በተቀናጀ መልኩ ወደ ትግበራ መለወጥ ወሳኝ መሆኑን አሁን እየተከሰቱ ያሉት አሳዛኝ ሁኔታዎች እንደሚያመለክቱም ገልጿል።

በመሆኑም፣ በያዝነው ዓመት መሰል አደጋዎቹ የመከሰት እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የጥናትና ምርምር ውጤቶችን መሠረት በማድረግና ቅንጅታዊ አሰራርን በመከተል የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎችን በተግባር እንዲያከናወኑም ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

በደቡባዊ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መሰል አደጋዎች ሲከሰቱ የአሁኑ የመጀመሪያው ሳይሆን ከስድስት ወራት እና ከአንድ ዓመት በፊት በተመሳሳይ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ተከስተው ከ500 በላይ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡‎

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *