በኢትዮጵያ በአጋቾች ታግቶ የቆየው ኬንያዊ ዜጋ 3 ሚሊየን ሽልንግ ከተከፈለ በኋላ መለቀቁን ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ አስታወቁ።
የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር እና በአዲስ አበባ ያሉት አምባሳደራቸው ባደረጉት ጥረት 3 ሚሊየን የኬንያ ሽልንግ ለአጋቾች ከተከፈለ በኋላ ሳሙኤል ንጃጊ የተባለው ዜጋቸው መለቀቁን ገልፀዋል።
ሳሙኤል ከሳምንት በፊት በደብረ ብርሃን ከተማ ተቀጥሮ ከሚሰራበት ድርጅት ታግቶ የተወሰደ ሲሆን የኬንያ ኤምባሲ ለኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን ካሳወቀ በኋላ ድርድሮች መደረጋቸው ተዘግቧል።
ዊሊያም ሩቶ 3 ሚሊየን የኬንያ ሽልንግ በአጋቾች መጠየቁን ገልፀው ሳሙኤል ይሰራበት የነበረው ድርጅት ክፍያውን መክፈሉን ገልጸዋል።
ሳሙኤል ከተለቀቀ በኋላ አዲስ አበባ በሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ መቆየቱንና ወደ ኬንያ ሄዶ ከቤተሰቦቹ ጋር መቀላቀሉ ሲነገር ሩቶ ዜጎች የሚሰሩባቸው የውጪ ሃገር ድርጅቶች እንደ ሳሙኤል ሁሉ ከታወቀ መንግስት አስፈላጊዉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ይሁንና ኬንያዊው በማን እንደታገተ እና ተቀጥሮ ሲሰራ የነበረበት ድርጅት አልተጠቀሰም።
በኢትዮጵያ በየጊዜው በሚያጋጥሙ የጽጥታ ችግሮች ምክንያት የዜጎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ መብቶች እየተገደበ ይገኛል።
እገታው የተፈጸመበት ስፍራ ከአዲስ አበባ በ160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን በአንጻራዊነት የተሻለ ደህንነት የሚታይበት ስፍራ ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ አደራጃለሁ ካለበት ጊዜ ጀምሮ በአማራ ክልል በመንግስት እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ የአፍሪካ ህብረት እና አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ ምዕራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ በተደጋጋሚ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቆም ለመደራደር ዝግጁነቱን ቢገልጽም እስካሁን ጥሰቶቹን ማስቆም አልተቻለም።
ህግ ውጪ ግድያ መፈጸም፣ ንብረት መዝረፍ እ፣ ንብረት ማውደም፣ የተራዘመ እስር፣ እገታ እና ከህግ ውጪ እስር እየተፈጸሙ ካሉ የዜጎች ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መካከል ዋነኞቹ እንደሆኑ መየሰብዓዊ መብት ተቋማት በተደጋጋሚ ያወጧቸው ሪፖርቶች ያስረዳሉ።