ኢትዮጵያና ጅቡቲ ሁለተኛውን የኃይል መስመር ዝርጋታ ስምምነት ተፈራረሙ

የኢትዮጵያን ጋላፊ ማከፋፈያ ጣቢያ ከጅቡቲው ናጋድ ማከፋፈያ ጣቢያ ጋር በሚያገናኘው በዚህ ፕሮጀክት፤ የ230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ እንደሚከናወን በጅቡቲ በተካሄደው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገልጿል፡፡

በጅቡቲ ግዛት የሚዘረጋውን 190 ኪሎ ሜትር ጨምሮ በአጠቃላይ 292 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የኃይል መስመር ፕሮጀክት በ18 ወራት ለማጠናቀቅ እቅድ መያዙ ተዘግቧል፡፡

ዓለም ባንክ ዝርጋታውን በ55 ሚሊዮን ዶላር ብድር የሚደግፈው ሲሆን፤ የግንባታ ውሉ ትራንስሬይል ሊሚትድ ለተሰኘ የህንድ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ መሰጠቱን ስፑትኒክ ዘግቧል፡፡

የጅቡቲ የኢነርጂ እና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዮኒስ አሊ ጉዲ፤ “ፕሮጀክቱ ታዳሽ የኃይል ሀብቶችን በመጠቀም ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ የኃይል ፖሊሲ እንድንተገብር ይረዳናል፣ ይህም 100 በመቶ የንጹህ ኃይል ግባችንን እንድናሳካ ያስችለናል” ሲሉ ተናግረዋል።

የኃይል መስመር ዝርጋታው የጅቡቲና ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የኃይል ትብብር አካል ሆኖ እ.ኤ.አ በ2013 የተጠነሰሰ ፕሮጀክት መሆኑን ዘገባው አስታውሷል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ጅቡቲን ጨምሮ ለኬንያ፣ ሱዳን እና ታንዛኒያ ሀይል በመሸጥ ላይ ስትሆን ለሌሎች ሀገራት ሀይል ለመሸጥ በዝግጅት ላይ መሆኗ ተገልጿል።

ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል ለመግዛት የአዋጭነት ጥናት በመካሄድ ላይ ሲሆን ቡሩንዲም ከኢትዮጵያ ሀይል የመግዛት ፍላጎት እንዳላት አስታውቃለች።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *