አምስት ፓርቲዎች የመሰረቱት ‘ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት’ የተሰኘው ቅንጅት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸሙት ጥቃቶች እንዲመረመሩ ለዓለማቀፉ ማሕበረሰብ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ቅንጅቱ በቅርቡ በአርሲ የተፈጸመውን ግድያ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤“ በኢትዮጵያ የሚፈጸሙት ማንነትና ሃይማኖት ተኮር ጥቃቶች መንግሥታዊ መዋቅርን የተከተሉ፣ ሥርዓታዊና ተጨማሪ እጅ ያለበት ስለመኾኑ ምርመራ እንዲደረግ ” ጥሪውን አቅርቧል።
ቅንጅቱ፤ “ጠያቂም ተጠያቂም ባለመኖሩ መግደል ቀላል ኾኗል” በሚል ያወጣው መግለጫ፤ “ እንዲህ ዓይነቱን ግዙፍ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት” በጽኑ እንደሚያወግዝ አስታውቆ፣ “እልቂት የየቀን ገጠመኙ ለኾነው የአካባቢው ማኅበረሰብም” ብርታትና መጽናናትን ተመኝቷል።
መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ እናት ፓርቲ፣ አዲሲ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አኢዴፓ) እና አማራ ግዮን ንቅናቄ ( አግን) የመሠረቱት ‘ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ‘ የተሰኘው ቅንጅት፤ ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ ባሻገርም ለአርሲ ዞን ነዋሪዎች፣ ሃይማኖት አባቶች፣ ለሚዲያ ሃላፊዎች፣ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ለሚገኙ ባለስልጣናትም ጥሪ አስተላልፏል።
ለነዋሪዎቹ ‘ ራሳቸውን እንዲጠብቁ ‘፤ ለሃይማኖት አባቶች ‘ ለሕዝቡ ጥሪ በማድረግ አባታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡም’ ጠይቋል።
የመንግሥት ባለሥልጣናት ደግሞ ‘ ከተጠያቂነት አታመልጡም ‘ ሲል ቅንጅቱ አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ አርሲ ዞን ወረዳዎች በንጹሀን ላይ በተፈጸመው ግድያ ይቅርታ እንዲጠይቅ እና ካሳ እንዲከፍል መጠይቁ ይታወሳል።
ኢሕአፓ በምዕመኑ ላይ የተፈጸመው ግድያና አካላዊ ጉዳትን አውግዞ መንግስት ንጹሀንን ከጥቃት መጠበቅ ባለመቻሉ ተጠያቂነቱን እንዲያምን እና ወንጀሉን የፈጸሙት አካላት በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡም አሳስቧል፡፡
ለደረሰው ግድያና አካላዊ ጉዳት የተሰማውን ሐዘን የገለጸው ፓርቲው መንግስት ይቅርታ እንዲጠይቅና አስፈላጊ ያለውን ካሳ ለሚመለከታቸው ሁሉ እንዲከፍል ሲልም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ከጥቂት አመታት ወዲህ የተባባሱት መጠነ-ሰፊ በዕምነትና በዘር ልዩነት ላይ የተመሠረቱ ግድያዎች፤ አፈናዎች፣ እገታዎች፣ ማፈናቀሎች፣ የንብረት ንጥቂያዎችና ውድመቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙም ፓርቲው በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤት ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በግድያው ዙሪያ ባወጣው መግለጫ መንግስት የዜጎችን የመኖር መብት እንዲያረጋግጥ መጠየቁ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ምክር ቤት በበኩሉ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ወረዳዎች በተፈጸመው የንጹሀን ግድያ ማዘኑን ገልጾ መንግስት የህግ የበላይነት እንዲያስከብርም ጠይቋል።
የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥታት እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ ያሉት አስተያየት ባይኖርን የዞኑ አስተዳድር ግን የተባለው ግድያ አለመፈጸማቸውን አስታውቋል።