ብሔራዊ መታወቂያ ተመዝጋቢዎችን ወደ 63 ሚሊዮን ለማድረስ መታቀዱ ተገለጸ

ኢትዮጵያ ሚያዝያ 2015 ላይ ነበር ብሔራዊ መታወቂያ በሙከራ ደረጃ መመዝገብ የጀመረችው፡፡ በ29 ከተሞች የተጀመረው ይህ ፕሮግራም ከታህሳስ 2014 ጀምሮ ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ ለማካሄድ በይፋ ተጀምሯል፡፡

ኢትዮ ነጋሪ ይህ የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ ምን እንደሚመስል በሀገሪቱ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ነዋሪዎችን እና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላትን አነጋግሯል፡፡

አቶ አማረ አሰፋ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ አጣዬ ከተማ ከሀገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ በ300 ኪሎ ሜትር በሰሜን ኢትዮጵያ በኩል የምትገኝ ከተማ ናት፡፡

የድጅታል መታወቂያ ካሳለፈነው ሚያዝያ ወር ጀምሮ መሰጠት መጀመሩን ገልጸው ከሁለት ወር በፊት የድጅታል አይዲው ታትሞ እጃቸው እንደገባ ነግረውናል፡፡ አሁን ላይ በአጣዬ ከተማ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ፣ በከተማ ምግብ ዋስትና የታቀፉ ተረጂዎች እርዳታ ለማግኘት እና ጡረተኞች ደመወዛቸውን ለመቀበል የድጅታል መታወቂያ ማውጣት ግዴታ ሆኗልም ብለዋል፡፡

መጀመሪያ አካባቢ መታወቂያው ወዲያው እየታተመ ቢደርሰንም ቀስ በቀስ ግን ወረፋው እየጨመረ ነው እስከ 4 ወር ለመጠበቅ ተገደናል፡፡ አገልግሎቱ በአጣዬ ከተማ በሁለት ቦታዎች የብሔራዊ መታወቂያ እየተሰጠ ቢሆንም አብዛኛው የወረዳው ነዋሪ በሚኖርባቸው የገጠር ቀበሌዎች ላይ ግን እስካሁን አልተጀመረም ብለዋል፡፡

አቶ እድል ወርቁ በትግራይ ክልል ውቅሮ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ አቶ እድል እንዳሉን ከሆነ አቶ እድል የብሔራዊ መታወቂያ እንዳላወጡ ነግረውን በከተማው ውስጥ በተለይም በኢትዮ ቴሌኮም ቅርንጫፍ ቢሮ እና በአንድ የግል ባንክ ቀርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ምዝገባው እየተካሄደ መሆኑን አውቃለሁ ብለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ በ800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ውቅሮ ከተማ በተለይም የፌደራል ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ብሔራዊ መታወቂያን እንደ ግዴታ እንደሚጠይቁ የገለጹት ነዋሪው ሌሎች የትግራይ ክልል አገልግሎት ሰጪዎች ግን ብሔራዊ መታወቂያን እንደ ግዴታ እንደማይጠይቁም ተናግረዋል፡፡

በምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል የምትገኘው በጋምቤላ ክልል ዲማ ከተማ የሚኖሩ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌላኛው ነዋሪ በበኩላቸው በዲማ ከተማ የብሔራዊ ድጅታል መታወቂያ ምዝገባ እስካሁን እንዳልተጀመረ ተናግረዋል፡፡

ዲማ ከተማ ከክልሉ ዋና መቀመጫ ጋምቤላ ከተማ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን ከአዲስ አበባ ደግሞ በ570 ኪሎ ሜትር ትርቃለች፡፡ የከተማዋ እና አካባቢው ነዋሪ ለተለያዩ አገልግሎቶች ወደ ጋምቤላ ከተማ ሲሄድ እግረ መንገዱን የድጅታል መታወቂያ ምዝገባ እንደሚያካሂድም ነዋሪው አክለዋል፡፡

በረከት በቀለ የአዲ አበባ ነዋሪ ሲሆን ብሔራዊ መታወቂያ ከተመዘገበ አንድ ዓመት እንደሞላው ተናግሯል፡፡

እንደ በረከት ገለጻ አሁን ላይ ብዙ አገልግሎቶችን ለማግኘት የግድ ብሐየራዊ መታወቂያ መያዝ ግዴታ በመሆኑ ሁሉም ሰው መታወቂያውን ለመያዝ እየተመዘገበ መሆኑንም ገልጿል፡፡ መታወቂያው ቀላል፣ ለ10 ዓመት የሚያገለግል መሆኑ፣ በሁሉም ቦታዎች ተቀባይነት ያለው መሆኑ እና በመታወቂያው ላይ የዜጎችን ብሔር ስለማይጠቅስ ለመንቀሳቀስ ጥሩ እንደሆነ ነገር ግን የመረጃችን ደህንነት አስተማማኝነት ላይ የተወሰነ ስጋት እንዳለው ጠቅሷል፡፡

የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዮዳሄ ዘሚካኤል እንዳሉት በተያዘው የ2018 በጀት ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ ፋይዳ ድጅታል መታወቂያ ያላቸው ዜጎችን ቁጥር 63 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዷል ብለዋል፡፡

ፕሮግራሙ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ 23 ሚሊዮን ዜጎች ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ እንደወሰዱ የገለጹት አቶ ዮዳሄ በዚህ ዓመት ብቻ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች ለሚገኙ 40 ሚሊዮን ዜጎች ፋይዳ ድጅታል መታወቂያ የመስጠት ስራው እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስራ አስኪያጁ አክለውም አገልግሎቱ ከዚህ በፊት በከተሞች እና በተወሰኑ ማዕከላት ብቻ ሲሰጥ እንደነበር ገልጸው ተጨማሪ የምዝገባ ማሽኖች እና ማዕከላት ወደ ስራ መግባታቸውንም ተናግረዋል፡፡

እንደ ባንክ ቅርንጫፍ ቢሮዎች፣ የኢትዮ ቴሌኮም ቢሮዎች፣ ፖስታ ቤቶች እና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ብቻ ሲሰጥ የነበረው የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ አሁን ላይ ተጨማሪ ማዕከላት እንደተቋቋሙም ስራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት የተሰጠው ከ20 ሚሊዮን ባልበለጠበት በአንድ ዓመት ውስጥ እንዴት ለ40 ሚሊዮን ዜጎች ፋይዳ ድጅታል መታወቂያ ልትሰጡ አስባችኋል? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ “ከዚህ በፊት ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያን ስንሰጥ የነበረው ከተሞች ላይ ብቻ ነበር፣ አሁን ግን የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ቁጥር ከመጨመር ባለፈ ወደ ገጠራማ ቀበሌዎች ሳይቀር እየሄድን ዜጎችን ለፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ መመዝገብ ተጀምሯል ይህን አስፍተን እየሰራንበት ነው፣ ለዚህ ነው ብዙ አስፍተን ያቀድነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በገጠር አካባቢዎች ያሉ የመንግስት አደረጃጀቶችን፣ የቀበሌ ጽህፈት ቤቶች፣ የሴፍቲ ኔት ማዕከላት ላይ የፋይዳ ድጅታል መታወቂያ ምዝገባ ማድረግ ጀምረናል ያሉት አቶ ዮዳሄ መብራት እና መንገድ በሌለባቸው ቀበሌዎች ሳይቀር ምዝገባ እያካሄድን ነውም ብለዋል፡፡

ስራ አስኪያጁ አክለውም የድጅታል መታወቂያ ምዝገባውን ከመንግስት ተቋማት ባለፈ ሱፐር ኤጀንቶችን በመጠቀም ምዝገባ እያካሄዱ መሆኑን ገልጸው ዜጎች የግዴታ ምዝገባ ካላካሄዱ አገልግሎቶችን እንደማያገኙ ገደብ መጣሉ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሲቪል ምዝገባ የሚያካሂዱ የመንግስት ተቋማት የብሔራዊ ድጅታል መታወቂያ ምዝገባ እንዲያደርጉ መደረጉም ተገልጿል፡፡

ፋይዳ ድጅታል መታወቂያ ካልያዛችሁ አገልግሎት አንሰጥም ሲሉ የነበሩት የፌደራል ተቋማት ብቻ ነበሩ የተባለ ሲሆን አሁን ላይ የክልል አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ድጅታል መታወቂያን እንደ ግዴታ እያስቀመጡ በመሆኑ በዚህ ዓመት ለመመዝገብ የተያዘው የ40 ሚሊዮን ዜጎች ምዝገባ እቅድ እንደሚሳካም አቶ ዮዳሄ ተናግረዋል፡፡

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ በ2019 ዓ.ም ብሔራዊ መታወቂያ ያላቸው ዜጎችን ቁጥር ከ70 ሚሊዮን በላይ ለማድረስ የታቀደ ሲሆን ወደ ገጠራማ አካባቢዎች በተሄደ ቁጥር የተመዝጋቢዎች ቁጥር እየቀነሰ እንደሚመጣ ይጠበቃል፡፡

ሁሉንም ዜጋ የብሔራዊ ድጅታል መታወቂያ መመዝገብ እንደማይቻል የገለጹት ስራ አስኪያጁ ከባንክ አገልግሎት፣ ከቴሌኮም አገልግሎት፣ ከግብር ስርዓት ውጪ የሆኑ እና ተቀጥረው የማይሰሩ ሰዎችን ወደ ድጅታል ብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ እንዲመጡ ማድረግ እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡

እነዚህን ዜጎች ወደ ብሔራዊ ድጅታል መታወቂያ ምዝገባ ስርዓት ለማምጣት የተለየ እና ሌላ እቅድ ማቀድ እንደሚገባም ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

እንደ አሜሪካ ያሉ ከ150 ሀገራት በላይ ልምድ ያላቸው የበለጸጉ ሀገራት ሁሉንም ዜጎቻቸውን ብሔራዊ ድጅታል መታወቂያ መስጠት እንዳልቻሉ የገለጹት አቶ ዮዳሄ ከመንግስት ተቋማት አገልግሎት የማይፈልጉ እና ከሀገሪቱ ድጅታል ስርዓት ላይ ምንም አይነት አገልግሎት የማይጠቀሙ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ዮዳሄ አክለውም ብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ ዋናው ዓላማ ዜጎች የተቀናጀ እና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ዜጎች ለፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ ሲጠየቁ ፈቃደኛ እንደሆኑ የሚገልጹት አቶ ዮዳሄ መረጃቸው አስተማማኝ እና ለሶስተኛ ወገን ተላልፎ እንደማይሰጥም ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ባለው መረጃ ከዜጎች እየቀረበልን ያለው ጥያቄ የምዝገባ ቦታዎቹ እንዲሰፉ ፣ የደህንት ጥበቃው ምን ያህል ነው እና የመታወቂያ ህትመት እንዲፋጠን የሚሉ ናቸው ተብሏል፡፡

ብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ አገልግሎቶችን ከማቀላጠፍ ባለፈ የዜጎችን የእርስ በርስ ግንኙነት የበለጠ የሚያቀራርብ መሰረተ ልማት መሆኑም ተገልጿል፡፡

አንዳንድ ዜጎች የተጭበረበረ ድጅታል መታወቂያ (አይዲ) ይዘው መገኘታቸውን የገለጹት አቶ ዮዳሄ ዜጎች ጥራት የሌለው የድጅታል መታወቂያ ከመያዝ እንዲቆጠቡም እቶ ዮዳሄ አክለዋል፡፡

ጥራቱን የጠበቀ ብሔራዊ መታወቂያ በኢትዮ ቴሌኮም እና ፖስታ ቤት በኩል እንዲሁም በብሔራዊ መታወቂያ ድረገጽ በኩል በማዘዝ መያዝ ይቻላል የተባለ ሲሆን ጥራቱን እስከጠበቀ ድረስ በግል ማተሚያ ቤቶች በኩል በማሳተም መያዝ እንደሚቻልም ተገልጿል፡፡

ይሁንና ድጅታል መታወቂያውን አሳትሞ ወይም በዲጂታል ኮፒ መያዝ ተመሳሳይ የህጋዊነት እድል አላቸውም ተብሏል፡፡

ፋይዳ ድጅታል መታወቂያ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች በፍትሀዊነት እየተሰጠ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን የመመዝገቢያ ማዕከላትን ከ5 ሺህ ወደ ሰባት ሺህ መድረሱ ተገልጿል፡፡

የብሄራዊ መታወቂያ ምዝገባውን በዚህ ዓመት በስፋት ለመስጠት መታቀዱን ተከትሎ ተጨማሪ ሶስት ሺህ የምዝገባ ማዕከላትን በመጨመር ከሁለት ወራት በኋላ ወደ 10 ሺህ የማድረስ እቅድ መኖሩንም ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

ብሔራዊ መታወቂያ የተመዘገቡ ሰዎች የስም ስህተት ወይም ሌሎች የመረጃ ስህተቶች ካሉ ማስተካከል ይቻላል የተባለ ሲሆን ስህተቱ የተፈጸመው ተመዝጋቢ ግለሰቦች በሰጡት መረጃ ከሆነ ለማስተካከል የቅጣት ክፍያ ይኖራል የተባለ ሲሆን ስህተቱ በመንግስት ተቋማት የተፈጸመ ከሆነ ግን ስህተቱን በነጻ ማስተካከል እንደሚቻል አቶ ዮዳሄ ተናግረዋል፡፡

ስህተቶቹን ለማረምም ብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ በሚካሂዱ ተቋማት በመሄድ አልያም ባሉበት ሆነው በብሄራዊ መታወቂያ ድረገጽ ላይ በመግባት ማስተካከል እንደሚቻል ተገልጿል፡፡

የፋይዳ ድጅታል መታወቂያ ካርድ የአገልግሎት ጊዜ እስከ 10 አመት እንዲያገለግል ታስቦ ተዘጋጅቷል የተባለ ሲሆን በጊዜ ሂደት አሻራን ጨምሮ ባዮሜትሪክ መረጃዎች በረጅም ጊዜ ውስጥ የሚቀየሩ በመሆኑ በ15 በ20 እና በ10 አመታት ውስጥ መረጃዎችን ለማደስ መታቀዱ ተገልጿል፡፡

ይሁንና ይህን የመረጃ ማደስ ስራ ለመስራት እስካሁን የወጣ ህግ ባይኖርም ከስምንት አመት በኋላ ዜጎች መረጃ ዳግሞ መስጠት ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል አቶ ዮዳሄ ገልጸዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *