ቢሊየነሩ አሊኮ ዳንጎቴ በኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ተስማማ

የአፈር ማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት መፈረሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በዓመት እስከ ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ማምረት የሚያስችል መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት መፈረሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “ወደ ምግብ ዋስትና እና የግብርና ሽግግር በምናደርገው ጉዞ አንድ ሌላ እጥፋት ላይ በመድረሳችን ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንኳን ደስ አለን!” ብለዋል።

2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚፈስበት ይህ ሜጋ ፕሮጀክት በዓመት እስከ ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ የሚያመርት ሲሆን፤ “ይህም ኢትዮጵያን ከዓለም ግንባር ቀደም አምራቾች አንዷ ያደርጋታል” ብለዋል።

“ፕሮጀክቱ በሀገር ውስጥ የሥራ እድል ይፈጥራል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ “ለዘመናት ለተፈተኑት ገበሬዎቻችን አስተማማኝ የማዳበሪያ አቅርቦት ያረጋግጣል። ለምግብ ሉዓላዊነት መንገዳችንም ወሳኝ ርምጃ መውሰዳችንን ያመላክታል” ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም፤ “በመላው አህጉሩ ኢትዮጵያ ያላትን ተወዳዳሪነት በማጠናከር ሕዝባችንን እና ነጋችንን የሚጠቅሙ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንቶችን የመከወን ጽኑ አቋማችንን ያሳያል” ብለዋል።

የዛሬውን የፊርማ ስምምነት ተከትሎ ፋብሪካው በሚቆምበት ስፍራ ፕሮጀክቱን በይፋ እንደሚጀመር የገለጹም ሲሆን፤ “ይህን ታሪካዊ ጉዞ ጀምረናል። ለገበሬዎቻችን፣ ለኢኮኖሚያችን እና ለኢትዮጵያ ነገ ስንል እንጨርሰዋለን” ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዓመት ለአፈር ማዳበሪያ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የምታወጣ ሲሆን ፋብሪካ በሀገር ውስጥ ለመገንባት ከ10 ዓመት በፊት ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም እስካሁን እውን መሆን አልቻለም፡፡

የአፍሪካ ቁጥር አንድ ባለጸጋ የሆነው ናይጀሪያዊው አሊኮ ዳንጎቴ በኢትዮጵያ ሲሚንቶ ፋብሪካ ያለው ሲሆን የአፈር ማዳበሪያ እና የስኳር ፋብሪካዎችን የመገንባት እቅድ እንዳለው ከዚህ በፊት መናገሩ ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *