ኢትዮጵያ ብሔራዊ የውትድርና ፖሊሲ አጸደቀች

ዕድሜያቸው 18 ዓመት የሞላቸውና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ወታደራዊ ስልጠና ወስደው ለሁለት ዓመት ብሔራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል አዲስ አዋጅ ፀድቋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት አዋጅን አጽድቋል።

ምክር ቤቱ ከትናንት በስቲያ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ መንግስት አዘጋጅቶ ያቀረበውን የተሻሻለ የመከላከያ ሰራዊት ረቂቅ አዋጅ አጽድቋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ዲማ ነገዎ እንደተናገሩት፤ ተማሪዎች በፈቃዳቸው በመደበኛ መከላከያ ሰራዊት ወይም የብሔራዊ ተጠባባቂ ሃይል አባል የሚሆኑ ከሆነ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ተያያዥ መብቶችንና ጥቅሞች እንዲጠብቁላቸው ያደርጋል ብለዋል፡፡

በመንግስት ተዘጋጅቶ የቀረበው የተሻሻለ የመከላከያ ሰራዊት ረቂቅ አዋጅ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ የተጣለበትን ሀገርን የመጠበቅ ተልክኮ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመወጣት እንዲችል ያደርገዋል ተብሏል፡፡

በመንግስት የተሻሻለውና በምክር ቤቱ የፀደቀው ይህ አዋጅ የሰራዊቱ አባላት የጡረታ መውጫ የእድሜ ጣሪያ አወሳሰን እንዲሁም የአገር ህልውና ከባድ አደጋ ላይ በሚወድቅ ጊዜ ከሰራዊቱ የተገለሉ አባላት መቀጠር የሚችሉበትን ሁኔታ ሁሉ አካቶ መያዙም ተገልጿል፡፡

ይሁንና ይህ ብሔራዊ የውትድርና ህግ አስገዳጅ ሳይሆን በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ነው ተብሏል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን እንደመጡ የብሔራዊ ውትድርና ፖሊሲ ሊያወጡ እንደሚችሉ ተናግረው ነበር።

ኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች የነበሩ የልዩ ሀይል አባላትን ወደ መከላከያ ሰራዊት እንዲቀላቀሉ መወሰኗ ይታወሳል፡፡

ይህን ተከትሎም አሁን ላይ የክልል ልዩ ሀይል የፈረሰ ሲሆን በአማራ ክልል ልዩ ሀይሉ ለምን ይፈርሳል የሚል ህዝባዊ ተቃውሞዎች ተደርገዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *