በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው እንደሆነ የተገለጸ የብረን ማዕድን በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ጊምቢ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለማውጣት ስምምነት ተፈርሟል፡፡
የማዕድን ሚኒስቴር በኢትዮጵያ እና ቻይናዊያን በተቋቋሙ ኩባንያዎች መካከል የብረት ማዕድን ልማት ፕሮጀክት ዛሬ ተፈራርሟል፡፡
1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ አለው የተባለው ይህ የ10 ዓመት የብረት ማዕድን ማውጣት ስምምነት የማዕድን ሚኒስቴር እና ዜድ ዋይ ቲቢ-ዲኤይኤም ስቲል ማኑፋክቸሪንግ ከተሰኘ የግል ኩባንያ ጋር ስምምነት ፈጽሟል፡፡
የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ ከስምምነቱ በኋላ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የብረት ማዕድናት እንዳሏት ካወቀች ከ70 ዓመት በላይ ቢሆናትም “እስካሁን አንድም የብረት ማዕድን አለማውጣቷን” ተናግረዋል፡፡
“በወለጋ ጊምቢ ቢቂላል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ብረት እንዳለን የታወቀው በ1956 ነበር፣ ግን እንደምታውቁት እስካሁን አንድም ብረት ማዕድን አውጥተን መጠቀም አልቻልንም ” ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብረት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ቢኖሩም የብረት ማምረቻ ጥሬ እቃዎችን ከውጭ ሀገራት በውድ ዋጋ ገዝተው የሚያመጡ በመሆኑ አዋጭ ሊሆን እንዳልቻለም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለፈው ዓመት ይፋ ባደረገው የአምስት ዓመት እቅዱ ላይ በኢትዮጵያ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ቶን ብረት ማዕድን እንዳለ በተለያዩ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩ ገልጾ እስከ እ.ኤ.አ. 2030 ድረስ በዓመት ከሚያስፈልገው መጠን ውስጥ ሶስት ሚሊዮን ቶን ያህሉን በሀገር ውስጥ የማምረት እቅድ እንዳለ ገልጿል፡፡
ስምምነቱን የፈረመው ኩባንያ በኢትዮጵያዊ እና ቻይናዊ ኩባያዎች ጥምረት የተመሰረተ ሲሆን የ10 ዓመት ኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡ በሁለት ዓመት ጊዜ ዉስጥም ኩባንያው ግንባታውን ጨርሶ ወደ ምርት ሥራ እንደሚገባ ተገልጿል።
ኩባንያው በሚቀጥሉት 10 ዓመት ውስጥ 14 ነጥብ 7 ሚሊዮን ቶን ብረት ምርት ለማምረት መስማማቱ ሲገለጽ 10 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥር 26፣ 2018 ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ኢትዮጵያ በሁለት ዓመት ውስጥ ከውጭ የሚገቡ የብረት ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች እንደምትተካ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ሌላኛው በዛሬው ዕለት ከተካሄዱ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች መካከል የፖታሽ እና ወርቅ ማዕድን ልማት ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በአፋር ክልል ኪልባቲራስ ዞን፣ ዳሎል ወረዳ የፖታሽ ማዕድንን ለማልማት የ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ፈቃድ ከማዕድን ሚኒስቴር ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡
ለ20 ዓመት ይቆያል የተባለው ይህ የፖታሽ ማዕድን ኢንቨስትመንት ስምምነት በዳሎል ወረዳ የሚገኝ 365 ነጥብ 2 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለውን ቦታ ማዕድን ለማውጣት ፈቃድ ይሰጣል፡፡ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በሁለት ዓመት ጊዜ ዉስጥ የፋብሪካ ግንባታውን ጨርሶ ወደ ምርት ስራ ለመግባት ተስማምቷል፡፡
የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ከስምምነቱ በኋላ እንዳሉት መንግስታዊው ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የፖታሽ ማዕድኑ ኢንቨስትመንት የተፈራረመው ላለፉት ዓመታት በርካታ ኩባንያዎች ፖታሽ ማዕድንን ለማውጣት ቢሞክሩም ስኬታማ ባለመሆናቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በራሱ አልያም በሌሎች አማራጮች ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር በመሆን የፖታሽ ማዕድኑን በማልማት ለውጭ ገበያዎች እንደሚያቀርብም ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡
ይህ የፖታሽ ማዕድን ፕሮጀክት በመጪዎቹ 10 ዓመታት ውስጥ ከ24 ሚሊዮን ቶን በላይ ፖታሽ በማምረት 9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል፡፡
ሶስተኛው ስምምነት የ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር የወርቅ ማዕድን ማውጣት ሲሆን ቤሮ ማይኒንግ ኤንድ ትሬዲንግ የተሰኘ የሀገር በቀል ኩባንያ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ቤሮ ወረዳ የሚገኝ ነው፡፡ ቤሮ ማይኒንግ ለ19 ዓመታት የሚቆይ ፈቀድ የተሰጠው ሲሆን በሁለት ዓመት ጊዜ ዉስጥ የፋብሪካ ግንባታውን ጨርሶ ወደ ምርት ስራ ይገነባል ተብሏል፡፡