የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስፈጻሚ የኡጋንዳ አየር መንገድን እንዲመሩ ተሾሙ

አቶ ግርማ ዋቄ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬታማ እንዲሆን የአመራርነት ሚናቸውን ካሳረፉ ሰዎች መካከል ዋነኛው ናቸው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከለቀቁ በኋላ ወደ ኪጋሊ አምርተው የሩዋንዳ አየር መንገድን በማቋቋም አሁን ላይ በማደግ ላይ ካሉ የአፍሪካ አየር መንገዶች መካከል አንዱ ሆኗል።

ሌላኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ኡጋንዳ ኢትዮጵያዊውን የአቪዬሽን መሪ የሆኑት አቶ ግርማ ዋቄን ቀጥራለች።

አቶ ግርማ የኡጋንዳ አየር መንገድን በጊዜያዊነት ስራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙ ሲሆን በተጨማሪም የሀገሪቱን አቪዬሽን አማካሪ ሆነውም እንደሚያገለግሉ የትራንስፖርት ሚንስቴር ገልጿል።

የኡጋንዳ አየር መንገድ በ1985 ዓ .ም የተቋቋመ ቢሆንም በኪሳራ ምክንያት በ2009 ተዘግቶ ነበር።

ከስድስት ዓመታት በፊት ዳግም የተቋቋመው የኡጋንዳ አየር መንገድ በኪሳራ ላይ ካሉ የአፍሪካ አየር መንገዶች መካከል አንዱ ነበር።

አየር መንገዱን ሲመሩ የነበሩት ጀኒፈር ባሙቱራኪ ስልጣናቸውን ለአቶ ግርማ ዋቄ እንዲያስረክቡ የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ መወሰናቸው ተገልጿል።

ከአንድ ቢሊዮን በላይ ህዝብ ያለባት አፍሪካ 80 በመቶ የአየር ትራንስፖርት በመካከለኛው ምስራቅ እና አውሮፓ ሀገራት አየር መንገዶች ይሸፈናል።

የአፍሪካ ግዙፍ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ60 የአህጉሪቱ ከተሞች በመብረር ላይ ይገኛል።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጨማሪ የግብጽ፣ ኬንያ፣ ሞሮኮ እና ሩዋንዳ አየር መንገዶች ተፎካካሪ አየር መንገዶች ናቸው።

የዛምቢያ፣ ማላዊ እና አስካይ አየር መንገዶች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ድጋፍ ከኪሳራ ወደ ትርፍ የመጡ አፍሪካዊ አየር መንገዶች ናቸው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *