አየር መንገዱ እንደገለጸው ባለፈው ሃሙስ ጥር 21 ቀን 2018 ዓ.ም ለሊት በኒጀር ዋና ከተማ ኒያሚ አውሮፕላን ማረፊያ በደረሰው ጥቃት ሁለት የአስካይ አየር መንገድ ቦይንግ 737 አውሮፕላኖች ላይ መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።
ሁለቱ አውሮፕላኖች የኢትዮጵያ አየር መንገድ አጋር የሆነው የአስካይ አየር መንገድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት ከአውሮፕላን አከራዮች የተከራያቸው እና በኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን የተመዘገቡ ናቸው ተብሏል።
በአውሮፕላኖቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመገምገም የተላከው የቴክኒክ ቡድን ጉዳቱ መጠነኛ መሆኑን እንዳረጋገጠ የገለጸው አየር መንገዱ አውሮፕላኖቹ ተጠግነው በቅርቡ ወደ አገልግሎት እንደሚገቡ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሎሜ (ቶጎ) መቀመጫውን ካደረገው አስካይ አየር መንገድ ጋር የ40% የባለቤትነት ድርሻና የቴክኒክ አጋርነት አለው።
የአስካይ አውሮፕላኖች የሽብር ጥቃት ኢላማ የሆኑት የሀገሪቱ ጦር የተተኳሽ እና ሌሎች ወታደራዊ የጦር መሳሪያ መካዝኖች ከኤርፖርቱ አቅራቢያ በመገኘታቸው ነው ተብሏል።
በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ናቸው የተባሉ የሽብር ቡድኖች የሀገሪቱ ጦር ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።
የኒጀር ወታደራዊ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ የሽብር ቡድኖቹ ጥቃቱን ከፈረንሳይ እና አይቮሪኮስት መንግስታት ድጋፍ መሆኑን አስታውቋል።