ኢትዮጵያ በያዝነው የ2026 ዓመት የ6.3 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደምታስመዘግብ ቢተነበይም፣ በአገሪቱ እየታየ ያለው ፈጣን የከተሞች መስፋፋት በመኖሪያ ቤት፣ በመሠረተ ልማትና በመሠረታዊ አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ ሁኔታ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የከተማ ነዋሪዎች ላይ የኑሮ ውድነትን እያባባሰ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት የከተሞች መስፋፋት የሚታይባት አህጉር ስትሆን፣ የከተማ ነዋሪዎቿ ቁጥር በየዓመቱ ከ3.5 በመቶ በላይ እያደገ ይገኛል።
ኢትዮጵያም ለዚህ ፈጣን ዕድገት በምክንያትነት የሚጠቀሱት ከፍተኛ የውልደት መጠን እና ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት ዋነኛ ተዋናይ ናት።
ይህ ፍልሰት በመኖሪያ ቤት፣ በመሠረተ ልማትና በመሠረታዊ አገልግሎቶች ላይ ያለውን ፍላጎት በእጅጉ እንዲጨምር አድርጎታል።
የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጠን ደግሞ የቤት ኪራይንና የሌሎች አገልግሎቶችን ዋጋ በማናር የከተማ ኑሮን ለብዙዎች አስቸጋሪ እያደረገው ይገኛል ሲል የዓለም ባንክ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።
የመሠረተ ልማት ድክመት፣ የማከማቻ ተቋማት እጥረት እና ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ በከተሞች ያለውን የምግብ አቅርቦት ሰንሰለት ተጋላጭ አድርገውታል።
በዚህም ምክንያት የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ዓመታዊ የምግብ ዋጋ ግሽበት እስከ መስከረም 2025 ድረስ ከ10 በመቶ በላይ ሆኖ መቆየቱ ተጠቁሟል።
የከተማ ነዋሪዎች በረጅም የአቅርቦት ሰንሰለት ወይም ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ መሆናቸው፣ ለዓለም አቀፍ የንግድ መዋዠቆች ይበልጥ ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይህም በቀጥታ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበትን እያባባሰው ይገኛል።
የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ባወጣው አዲስ ሪፖርት መሰረት፤ የምግብ ዋጋ መጨመር ተጋላጭ ቤተሰቦች የሚመገቡትን የምግብ ዓይነትና መጠን እንዲቀንሱ እያስገደዳቸው ነው።
ይህ በተለይ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ሕፃናት ላይ የመቀንጨጭ እና የመንምን አደጋን በእጅጉ ይጨምራል።
በሕፃንነት ዕድሜ የሚከሰት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በአካላዊና በአእምሮአዊ ዕድገት ላይ ዘላቂ ጉዳት የሚያደርስ ሲሆን፣ ይህም ወደፊት አገሪቱ ሊኖራት የሚችለውን የምርታማነት አቅም ይገድባል ተብሎ ይፈራል።
የኢኮኖሚ ጥናቱ እንደሚያመለክተው፣ መንግሥት እንደ ስትራቴጂካዊ የእህል ክምችት ያሉ የፖሊሲ መሣሪያዎችን በመጠቀም የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠር ጥረት እያደረገ ይገኛል።
ይሁን እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በምርት ዕድገት፣ በማከማቻ ተቋማትና በከተማ መሠረተ ልማቶች ላይ ትይዩ ኢንቨስትመንት ማድረግ ወሳኝ መሆኑ ተመልክቷል።