ወ/ሮ ሃይማኖት ዘለቀ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንን እንዲመሩ ተሾሙ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 5ኛው ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛው መደበኛ ስብሰባ ወ/ሮ ሃይማኖት ዘለቀ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው እንዲሾሙ የቀረበለትን ረቂቅ መርምሮ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

ምክር ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው የተሿሚዋን የረዥም ዘመን የሙያ ልምድና የሥራ ብቃት ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑ ተመልክቷል።

ወ/ሮ ሃይማኖት ዘለቀ በመገናኛ ብዙኃንና በኮሙኒኬሽን ዘርፍ ሰፊ ልምድ ያላቸው ባለሙያ ሲሆኑ በተለይም በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ውስጥ ከሪፖርተርነት እስከ አርታኢነት በመሥራት ውጤታማ የሥራ ዘመን አሳልፈዋል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ውስጥ በሙያቸው ያገለገሉ ሲሆን በቀድሞው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትም በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች አገራቸውን አገልግለዋል።

ወደ አሁኑ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ከመምጣታቸው በፊት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት በምክትል ቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የኮሙኒኬሽን ዘርፍ ኃላፊ በመሆን ሲሠሩ ቆይተዋል።

ተቋሙን ለአንድ ዓመት ያህል ሲመሩ የነበሩት ዶክተር ሳምሶን መኮንን በግል ምክንያት ከሀላፊነት መልቀቃቸው ተገልጿል።

የሀላፊ ቶሎቶሎ መቀያየር ያጋጠመው የኢትዮጵያ ሚዲያ ባለስልጣን ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ አራት ሀላፊዎች ተቋሙን እንዲመሩ ተሾመዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *