በጋምቤላ ክልል እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ ኢሰመኮ አሳሰበ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኅዳር 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ በጋምቤላ ወረዳ (አቦል)፣ በጋምቤላ ከተማ እና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭትና የጸጥታ መደፍረስ ተከትሎ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና ሥጋቶችን እየተከታተለ መሆኑን አስታውቋል።

ኢሰመኮ ባሰባሰበው መረጃ በጋምቤላ ከተማ አስተዳደር የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አዛዥ የነበሩት ዋና ኢንስፔክተር ኡመድ ኡጁሉ መገደልን ተከትሎ በከተማውና በአካባቢው ባሉት ወረዳዎችና ቀበሌዎች ግጭት ተፈጥሮ በተለያዩ አከባቢዎች የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ መቆየቱን አስታውቋል፡፡

በዚህም ሳቢያ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና የአካል ጉዳት መድረሱን፣ የሰዎችን እና የመጓጓዣ አማራጮችን እንቅስቃሴ የሚገድብ የሰዓት እላፊ በክልሉ መንግሥት መጣሉን፤ ባንኮችንና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት ማተቋርጠዋል ብሏል።

በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭትና የሰላም መደፍረስ በፍጥነት በማስቆም በሰዎች በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት፣ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር፣ የንብረት፣ የሥራ እንዲሁም ሌሎች ሰብአዊ መብቶች ላይ ተጨማሪ ጥሰቶች እንዳይደርሱ ለመከላከል በቂ የጸጥታ አካላት በአስቸኳይ እንዲሰማሩ እንዲደረግ ኢሰመኮ አሳስቧል።

በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጠሩ ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስቆም፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና ወደፊት ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ለመከላከል የፌዴራሉ እና የክልሉ መንግሥታት ተገቢ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በአካባቢው ተሰሚነት ያላቸው የሀገር ሽማግሌዎችን እንዲሁም የሃይማኖት እና የማኅረሰብ መሪዎችን በማሳተፍ ውይይቶችና ዕርቆች እንዲካሄዱ እንዲሁም ከአጋር ድርጅቶችና ባለድርሻዎች ጋር በትብብር በመሥራት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ተገቢውን ሕክምና እና ካሳ እንዲያገኙ እና እንዲቋቋሙ ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በጋምቤላ ክልል የሚከሰቱ ግጭቶችና የሰላም መደፍረሶች በክልሉ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ለማሻሻል የሚደረጉ ጥረቶችንና እርምጃዎችን እየተፈታተኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢሰመኮ ጉዳዩን ከዚህ ቀደም ለፌዴራሉና ለክልሉ መንግሥታት የሰጣቸውን ምክረ ሐሳቦች በተሟላ ሁኔታ እንዲፈጸሙ ሲልም አሳስበዋል፡፡

በተለይም በግጭቶችና ጥቃቶች ላይ ተሳታፊ የሆኑ ቡድኖች እና ግለሰቦች ላይ ተገቢውን የወንጀል ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነት የማረጋገጥ ጥረቶችን የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንዲሁም የክልሉ የጸጥታ ተቋማት ግጭቶችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል ብቃት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባም ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *