ኤርትራ ከኢጋድ ለመልቀቅ ያሳለፈችውን ውሳኔ ዳግም እንድታጤነው ተጠየቀች

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ፤ የኤርትራ መንግሥት ከድርጅቱ የመውጣት ውሳኔ ያሳለፈው “ተጨባጭ ሃሳቦች ወይም በአይነተኛ ተቋማዊ ወይም የፖሊሲ ማሻሻያዎች ዙሪያ ተሳትፎ” ሳያቀርብ መሆኑን በማንሳት ቅሬታውን ገልጿል።

ኢጋድ ይህንን ውሳኔ በይፋዊ የቃል ማስታወሻ መግባቱን አረጋግጧል። ሆኖም ግን፣ ሴክሬታሪያቱ ለድርጅቱ የተላከው ማስታወሻ ከማንኛውም ቀደም ያለ ውይይት ውጪ መሆኑን ጠቁሟል።

ኤርትራ ለሁለት አሥርት ዓመታት ያህል በራሷ ፍላጎት አባልነቷን ካገደች በኋላ፣ እ.ኤ.አ. ሰኔ 2023 በተካሄደው 14ኛው የልዩ መሪዎች ጉባኤ ላይ በሁሉም አባል አገሮች በሞቃት አቀባበል ወደ ድርጅቱ ተመልሳ ነበር ብሏል።

በዚያን ወቅት፣ መመለሷ “ሁሉን አቀፍነት፣ የክልላዊ ወንድማማችነት እና የታደሰ ትብብር የጋራ ቁርጠኝነት” ማሳያ እንደነበር ድርጅቱ አስታውሷል።

ነገር ግን፣ ኢጋድ ከሰኔ 2023 ጀምሮ ኤርትራ በኢጋድ ስብሰባዎች፣ ፕሮግራሞች ወይም እንቅስቃሴዎች ላይ ስትሳተፍ እንዳልቆየች ገልጿል።

ሴክሬታሪያቱ በዚህ ጊዜ ሁሉ “ትዕግሥትና በጎ ፈቃድ” ሲያሳይ እንደቆየ እና ለገንቢ ተሳትፎ ክፍት እንደነበር አሳውቋል።

ምንም እንኳን ውጥረቱ ቢኖርም፣ የኢጋድ ሴክሬታሪያት ውሳኔውን የወሰደው “ምንም ዓይነት ውይይት ወይም የለውጥ ሀሳብ ሳያቀርብ ነው” በማለት ቢወቅስም፣ “ግንኙነቱን እንደሚቀጥል” አስታውቋል።

ኢጋድ የኤርትራ መንግሥት “ዉሳኔዉን እንደገና እንዲመለከት እና ለሰላም፣ መረጋጋት እና የክልሉን ልማት የሚረዱ የጋራ ግቦችን ለማራመድ ሙሉ በሙሉ በበጎ ፈቃድ ወደ ድርጅቱ እንድትመለስ ጥሪውን አቅርቧል።

‎ኤርትራ ከሰሞኑ ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) መውጣቷን የሀገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በይፋ መግለጿ ይታወሳል።

‎አስመራ ለኢጋድ ዋና ጸሐፊ በላከችው መልእክት፤ ለውሳኔው መነሻ የሆነው “ተቋሙ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ድክመት በማሳየቱ” እና በቀጣናው ጉዳዮች ላይ በሚጫወተው “ጎጂ ሚና” መሆኑን ገልጻለች።

‎ኤርትራ እ.ኤ.አ. በ1993 ኢጋድ እንደገና ሲዋቀር፣ ለቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ለኢኮኖሚ ትስስር መጠናከር እንደ ዋና መሣሪያ ሆኖ የሚያገለግል ተቋምን ለመገንባት ከሌሎች አባል ሀገራት ጋር በመስራት ወሳኝ ሚና እንደተጫወተች አስታውሳለች።

‎ይሁን እንጂ መግለጫው፣ በሂደት እና በተለይም ከ2005 ጀምሮ (እ.ኤ.አ)፣ ኢጋድ የቀጣናውን ህዝቦች ተስፋና ፍላጎት ከማሳካት ይልቅ፣ በተወሰኑ አባል ሀገራትና በተለይም በኤርትራ ላይ እንደ መጠቀሚያ መሣሪያ በመሆን ጎጂ ሚና ተጫውቷል ብሏል።

‎በእነዚህም ድርጊቶች ምክንያት አስመራ በጎርጎሮሳውያኑ ሚያዚያ ወር 2007 ከአባልነቷ ለመውጣት መገደዷን መግለጫው አክሎ አብራርቷል።

‎ኤርትራ ኢጋድ ለሪፎርም ያቀረበችውን ጥሪ ሰምቶ ያለፈውን ታሪኩን ያስተካክላል በሚል ተስፋ፣ በጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ 2023 አባልነቷን እንደገና አጠናክራለች።

‎ሆኖም፣ የሀገሪቱ  መንግሥት ተቋሙ ሕጋዊ ግዴታዎቹን መካድ ቀጥሏል ያለ ሲሆን፤ ይህም ጠቀሜታውንና ሕጋዊ ሥልጣኑን እያዳከመው መጥቷል ብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *