የቀድሞው የአደጋ ስጋት ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በሙስና ወንጀል በ13 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የቀድሞ ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ምትኩ ካሳ በከባድ የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ13 ዓመት ጽኑ እስራትና በ50 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
የፍትሕ ሚኒስቴር ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ፣ አቶ ምትኩ ከሌሎች ተባባሪዎች ጋር በመሆን የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን ከ601 ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴን ጨምሮ በርካታ የምግብ እርዳታ ቁሳቁሶችን ከመጋዘን በማውጣት ለተረጂዎች ሳይደርስ ለዱቄት ፋብሪካዎችና ለሌሎች በመሸጥ ለግል ጥቅማቸው እንዳዋሉ አስረድቷል።
በተጨማሪም፣ ከ472 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ በሕገ ወጥ መንገድ እንዲከፈል በማድረግ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሰዋል።
ፍርድ ቤቱ አቶ ምትኩ ካሳን በተጨማሪም፣ በሕገ ወጥ መንገድ ያገኙትን ገንዘብ ምንጩን ደብቀው ሕጋዊ አስመስለው በማቅረብ ወንጀል ከልጃቸው ወ/ሮ ሚልካ ምትኩ እና ከባለቤታቸው ወ/ሮ ሶፊያ ጀማል ጋር ተከሰው ጥፋተኛ መሆናቸውን ወስኗል።
በአቶ ምትኩ ልጆችና ባለቤታቸው ስም ተገዝተው የተገኙ ተሽከርካሪዎችና መኖሪያ ቤቶች መኖራቸው በክሱ የተጠቀሰ ሲሆን፤ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ በሌሎችም ተከሳሾች ላይ በየደረጃው የወንጀል ተሳትፏቸው በክሱ ተዘርዝሮ ተካትቷል።
በዚህም መሰረት፣ ባለቤታቸው ወ/ሮ ሶፊያ ጀማል የ8 ዓመት ከ4 ወር እስራት ሲፈረድባቸው፣ ልጃቸው ወ/ሮ ሚልካ ምትኩ ደግሞ የ5 ዓመት እስራት ተበይኖባቸዋል።