ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት ሀገራትን እንደሚጎበኙ አስታውቀዋል።
እንደ ኢንዲያ ቱዴይ ዘገባ ከሆነ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ ከታህሳስ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ፣ ጆርዳን እና ኦማንን ይጎበኛሉ።
ኢትዮጵያ እና ሕንድ ጥሩ ወዳጅነት ያላቸው ሲሆን ከ15 ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት ሞንማሆን ሲንግ በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ-ሕንድ ቢዝነስ ጉባኤ ላይ ተሳትፈው መመለሳቸው ይታወሳል።
ሁለቱ ሀገራት ረጅም እድሜ ያስቆጠረ የዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ያላቸው ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ የህንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ውስጥ ተሳትፈዋል።
የብሪክስ አባል የሆኑት ኢትዮጵያ እና ሕንድ በትምህርት ፣ ጤና፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ዙሪያ በመተባበር ላይ ናቸው ተብሏል።
ሕንድ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ነጻ የትምህርት እድል በስፋት ከሚሰጡ ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ስትሆን ከመጀመሪያ ድግሪ እስከ ሶስተኛ ድግሪ ድረስ በማስተማር ላይ ትገኛለች።
በአሁኑ ወቅት ከ650 በላይ ህንዳዊያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ከመድሀኒት ማምረት አንስቶ እስከ ጨርቃጨርቅና አይሲቲ አገልግሎት ድረስ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
ባለሀብቶቹ በአጠቃላይ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሀብት ከማፍሰሳቸውም በላይ በሺህ ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የስራ እድል መፍጠራቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያስረዳል።