ቦረናን ጨምሮ 85 በመቶ የሚሆነው በኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር አካባቢ ያለ ህዝብ በመጪው ዓመት ከባድ የድርቅና ረሃብ ስጋት እንደተጋረጠባቸው ተገልጿል።
በኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር ቦረና ኢትዮጵያ እና ማርሳቢት ኬንያ አካባቢ ዝናብ አጠር መሆኑና አልፎ አልፎ ሲዘንብም ጎርፍ የሚያስከትል መሆኑ ተነግሯል፡፡
ቮለንተሪ ሰርቪስ ኦቨር ሲስ(VSO)፣ ሆርን ኦፍ አፍሪካ ዴቨሎፕመንት ኢንሼቲቭ (HODI) ፣አውስትራሊያን ዴቨሎፕመንት ኮፕሬሽን እና ሴንተር ፎር ዴቨሎፕመንት ኤንድ ጉድ ገቨርነንስ የተሰኙ የሲቪል ማህበራት በአካባቢው ሲሰሩ የቆዩትን የመጀመሪያ ዙር ፕሮጀክት መዝጊያ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የVSO የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ተመስገን አለሙ የአትዮጵያ ኬንያ ድንበር ከግጭት፣ ከድርቅ እና ረሃብ ባለፈ አካባቢው የአደንዛዥ ዕፅ ፣ ህገ-ወጥ የሰው ዝውውር እና ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት የበዛበት አካባቢ ነው ብለዋል።
የሲቪል ማህበር ተወካዩ ቦረናና የኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር አካባቢ ያለውን የድርቅ፣ የግጭት እና እሱን ተከትሎ የሚመጣውን ረሃብ መንስኤ እና መፍትሔ በጥናት ለመንግስት ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
ሴንተር ፎር ዴቨሎፕመንት ኤንደ ጉድ ገቨርነስ ቦርድ ሰብሳቢና የኦሮሚያ ግብርና ምርምር አማካሪው አቶ አበራ ዴሬሳ በቦረና እና በኬንያ ድንበር አካባቢ ያለውን የድርቅ፣ የግጭት፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ለማስቀረት መንግስት የፖሊሲ አማራጮችን እንዲከተል መክረዋል፡፡
ባለሙያው በተለይ በኬንያና ኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ በሚደረግ የቤት እንሰሳት ዝውውር ድርቁን ተከትሎ ሪፍት ቫሊ ፊቨር የእንሰሳት በሽታ ከተከሰተ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሃገር የምትልከው ስጋ የሚታገድበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
ሴንተር ፎር ዴቨሎፕመንት ኤንድ ጉድ ገቨርነስ ቦርድ ሰብሳቢና የኦሮሚያ ግብርና ምርምር አማካሪው አቶ አበራ ዴሬሳ ቦረና ከሁለት አመት በፊት በተከሰተ ድርቅ ከሁለት ሚሊየን በላይ የቤት እንሰሳት ሞተው ነበር ያሉ ሲሆን መንግስት የከርሰ ምድር ውሃን ማዘጋጀት ላይ እንዲያተኩር አሳስበዋል፡፡
የሲቪል ማህበራቱ የኢትዮጵያ እና የኬንያ የመንግስት አካላት በአካባቢው ያለውን ችግር ለማስቆም ከአሁኑ የተሻለ እና ተቋማዊ የሆነ ሥራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ባለሙያው ድርቅ በሚመጣበት ወቅት የአካባቢው አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን ለመሸጥ ፍቃደኛ አለመሆናቸው ድርቁ የሚያመጣውን ጉዳት ለመቀነስ በሚሰራው ስራ ላይ አንዱ እንቅፋት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በድርቅ እና በግጭት ምክንያት በአትዮጵያና ኬንያ ድንበር አካባቢ ካሉ ሰዎች፣ 70 በመቶው በድህነት ውስጥ ያለ ነው ተብሏል።
የሲቪል ማህበራቱ የኢትዮጵያ እና የኬንያ የመንግስት አካላት በአካባቢው ያለውን ችግር ለማስቆም ከአሁኑ የተሻለ እና ተቋማዊ የሆነ ሥራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።