ኢትዮጵያ 78 በመቶ የሬሚታንስ ገቢዋን እንደምታጣ ተገለጸ

ሀገሪቱ ከሬሚታንስ ገቢ 35 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የማግኘት አቅም እንዳላት ተገልጿል

ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገራት በሕጋዊ መንገድ ከሚላክላት ገንዘብ (ሬሚታንስ) የምታገኘው ገቢ የሀገሪቱን አቅም 22 በመቶ ብቻ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በተለያዩ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች ጋር በመወያየት ላይ ናቸው፡፡

ከዚህ በፊት በተባበሩት አረብ ኢምሬት እና ሳውዲ አረቢያ ከተሞች ከኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች ጋር የተወያዩት ፕሬዝዳንቱ አሁን ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያይተዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከሬሚታንስ ገቢ እየተገኘች ያለው ገቢ 7.2 ቢሊየን ዶላር ብቻ ነዉ ብለዋል።

አቶ አቤ ሳኖ እንዳስረዱት፣ አሁን ካለው የገንዘብ ፍሰት ቀሪው 78 በመቶ የሚሆነው ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ እንዳልሆነም ተናግረዋል።

የዳያስፖራውን ሙሉ አቅም በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ግን፣ ኢትዮጵያ በዓመት ከ35 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከሬሚታንስ ገቢ ልታገኝ እንደምትችል አስታውቀዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ባንኩ ለውጭ የሚኖረው ማህበረሰብ ያለውን ትኩረት ለማሳየት፣ በ2018 ዓ.ም ለዳያስፖራው ማህበረሰብ 50 ቢሊዮን ብር ለማበደር ዝግጅት መደረጉን ፕሬዝዳንቱ አስታውሰዋል።

የተጠቀሰው ገንዘብ ለብድር አገልግሎቱ ለኢንቨስትመንት፣ ለመኖሪያ ቤትና አውቶሞቢል ግዥ የቀረበ ነው ተብሏል።

በውይይቱ ወቅት ፕሬዚደንቱ እንዳስታወቁት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በአገር ውስጥ ለሚያካሄዱት የቢዝነስ እንቅስቃሴ፣ ለመኖሪያ ቤትና መሰል ፍላጎቶች የ50 ቢሊዮን ብር የብድር አገልገሎት ተመቻችቷል ብለዋል፡፡

የብድር አገልግሎቱ በተያዘው የ2024/25 በጀት ዓመት ተፈጻሚ እንደሚሆንም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ባንኩ አገልግሎቱን ለማግኘት ጥያቄ ለሚያቀርቡ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ቀልጣፋና ምቹ አሰራር እንደሚተገብርም አቶ አቤ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተባበሩት አረብ ኢምሬት ከተሞች አቡ ዳቢ እና ዱባይ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ገንዘባቸውን በቀላሉ ወደ ሀገራቸው እንዲልኩ ቦቲም ከተሰኘው የገንዘብ ማስተላለፊያ መተግበሪያ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት መፈጸማቸው ይታወሳል፡፡

እንደ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች መረጃ ከሆነ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሲሆን አብዛኞቹ በመካከለኛው ምስራቅ፣ አሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራት ይኖራሉ።

ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ ደቡብ አፍሪካ እና አሜሪካ ደግሞ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ይኖርባቸዋል።

የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዢ ማሞ ምህረቱ ከአንድ ወር በፊት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በአንድ ዓመት ውስጥ ከሬሚታንስ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአሜሪካ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ከተሞች ሆነው ህገወጥ የሬሚታንስ ገንዘብ ዝውውርን ይፈጽማሉ ያለቻቸውን ድርጅቶች ማስጠንቀቋ ይታወሳል።

ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መግለጫ በህገወጥ የውጭ ምንዛሬ ግብይት ውስጥ ያሉ አካላት ከድርጊታቸው ካልታቀቡ አካውንት ከመዝጋት ጀምሮ ገንዘባቸው እንደሚወረስም ተገልጿል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *