ከተሽከርካሪዎች የሚወጣ በካይ ጋዝ የሚቆጣጠር መመሪያ ተዘጋጀ

‎በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢኒስቲትዩት የተዘጋጀው፤ ከተሽከርካሪዎች የሚወጣን ጎጂ የካይ ጋዝ ልቀት ለመቆጣጠር የሚያገለግለው አስገዳጅ መመሪያ ከመስከረም 30 ቀን 2018 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል።

ዋነኛ ዓላማው የትራንስፖርት ዘርፉ ለበካይ ጋዝ ልቀት የሁለት ሦስተኛ ድርሻ ያለው በመሆኑ በጎጂ በካይ ጋዞች ምክንያት የሚከሰትን የአየር ብክለት መቀነስ ሲሆን፤ አዲሱ መመሪያ ሙሉ ለሙሉ ሲተገበር ተሽከርካሪዎች ወደ አየር የሚለቁትን የበካይ ጋዝ መጠን የሚቆጣጠር መሳሪያ እንዲገጥሙ ይገደዳሉ ተብሏል።

የተቋሙ የትራንስፖርት ዘርፍ የአየር ንብረት ክትትል እና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ግርማ ሳሙኤል፤ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ መመሪያው ከጸደቀበት መጋቢት 2017 ጀምሮ ውይይቶች ሲካሄዱበት እንደነበርም ተናግረዋል።

በዚህም አስገዳጅ መመሪያው ከጸደቀ በኋላ ከታክሲ ማኅበራት፣ ከክልል ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ላለፉት 6 ወራት ውይይት ሲካሔድበት መቆየቱን የአየር ንብረት ክትትል እና ቁጥጥር ቡድን መሪው ገልጸዋል። 

በካይ ጋዞችን የሚቆጣጠር መመሪያ ማዘጋጀት ያስፈለገው ከተሽከርካሪዎች የሚወጣው በካይ ጋዝ መጠን ከግዜ ወደ ግዜ በመጨመሩ ነው ተብሏል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ይፋ ባደረገው ጥናት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከተሸከርካሪዎች በሚወጣው በካይ ጋዝ ምክንያት በየዓመቱ ከ1,700 በላይ ሰዎችን ለመተንፈሻ አካላት ህመሞች እንደሚያጋልጥ ተነግሯል።

“የወጣው መመሪያ ተግባራዊነት ለመቆጣጠር የተለያዩ መንገዶች አሉ” ያሉት አቶ ግርማ፤ “የቦሎ እድሳት በሚካሄድበት የቴክኒክ ምርመራ ወቅት ተሸከርካሪው የበካይ ጋዝ ልቀት መከላከያ መሳሪያ መግጠሙ ይፈተሻል፣ በድንገት በሚካሄድ ፍተሻም ይረጋገጣል በተጨማሪም የበካይ ጋዝ ልቀት መከላከያ መሳሪያ መግጠሙን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ይሰጠዋል” ሲሉ አብራርተዋል።

የምንገኝበት መስከረም ወር ለተሽከርካሪዎች፣ ዓመታዊ የተሸከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ለሚሰጡ ተቋማት እና ለአጠቃላይ ማኅበረሰቡ የማስተማር እና የማሳወቅ ሥራ እንደሚሰራም አቶ ግርማ ነግረውናል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *