በሕገ ወጥ የወርቅ እና የገንዘብ ዝውውር 76 ተጠርጣሪዎች መያዛቸው ተገለጸ

በሕገ ወጥ የወርቅ፣ የገንዘብና የጦር መሣሪያ ዝውውር ተሳትፈዋል የተባሉ 76 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡

ፋና እንደዘገበው ከሆነ በተጠቀሱት የወንጀል ድርጊቶች ተሰማርተው በነበሩ የውጭ ሀገር ዜጎችና ኢትዮጵያውያን ላይ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ክትትል ሲደረግ ቆይቷል ተብሏል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የወርቅ ማዕድን በሕገ ወጥ መንገድ በማምረት፣ በመሰወርና በማዘዋወር፣ የሀገራችንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችን እንዲሁም ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎችን በማዘዋወር ወንጀሎች ላይ ተሳታፊ እንደነበሩ መግለጫው ጠቁሟል፡፡

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስና ከየክልሎቹ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ባካሄደው ልዩ ኦፕሬሽን እስካሁን 45 የውጪ ሀገር ዜጎች እና 31 የሀገር ውስጥ በድምሩ 76 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎች ላይ በተደረገ ብርበራ በሕገወጥ መንገድ የተከማቹ ግምታቸው ከ7 ኪሎ ግራም በላይ የወርቅ ምርቶችና ጌጣጌጥ፣ የወርቅ ማቅለጫና መመዘኛ መሣሪያዎች እንዲሁም አቅጣጫ ጠቋሚ ጂፒኤስ እና ማጠቢያ ኬሚካሎች ተይዘዋል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች ማለትም ከ19 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ የኢትዮጵያ ብር፣ 285 ሺህ 797 የአሜሪካ ዶላር፣ 207 ሺህ 910 ዩሮ፣ 16 ድርሀምና ሌሎች የተለያዩ የውጪ ሀገራት የገንዘብ ኖቶች እንዲሁም የተለያዩ ጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ግለሰቦቹ ለእዚሁ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ሲጠቀሙባቸው ተከማችተው የተገኙ ነዳጅ የያዙ በርካታ በርሜሎች፣ ጄነሬተሮች፣ ተሽከርካሪዎችና የተለያዩ ሀገራት ፓስፖርቶች፣ ላኘቶፖችና ሰነዶችን በኤግዝቢትነት ተይዘዋልም ተብሏል።

ይህ የወንጀል ድርጊት ሆን ተብሎ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለማዛባት እንዲሁም የዋጋ ግሽበት በማናር በማኅበረሰቡ ላይ ጫና በመፍጠር ኑሮውን ለማናጋትና የሀገራችንን ኢኮኖሚ አደጋ ላይ ለመጣል ታቅዶ ሲሰራ እንደነበረ አገልግሎቱ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የወንጀል መረቡን ለመበጣጠስ ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ተጨማሪ ክትትሎችንና ጥናቶችን በማድረግ ኦፕሬሽኑን መቀጠሉን ገልጾ፥ ይህንን በመረዳት ኅብረተሰቡ መሰል ሕገወጥ ድርጊቶችን በመጠቆም የተደራጁ ወንጀሎችን በመዋጋት ሂደቱ ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርቧል።

በተጨማሪም ሁሉም የክልል መስተዳደሮች ያለፌደራል መንግስት እውቅና እንዲሁም ያለኢሚግሬሽን ሕጋዊ የስራ ፈቃድ ማንኛውም የውጭ ሀገር ዜጋ በየትኛውም አካባቢ በመሰል የስራ ዘርፍ ላይ እንዲሰማራ ጊዜያዊም ይሁን ቋሚ ፈቃድ መስጠት እንደማይችሉ አስገንዝቧል፡፡

በዚህም ይህ አይነት ሕገወጥ ተግባርን በመከታተል የወንጀል ድርጊቱን በመከላከል ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱም ፖሊስ አሳስቧል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *