ቻይና ሰራሹ ሲኖ ትራክ ተሽከርካሪ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ተከለከለ

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከሲኖትራክ ምርት ተሽከርካሪዎች ጋር ተያይዞ በታየው የጥራትና ቴክኒክ ጉድለት ምክንያት፣ እነዚህ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ እገዳ መጣሉን አሳውቋል።

ይህ ውሳኔ በሰዎች ህይወት ላይ በተደጋጋሚ አደጋ እየደረሰ በመሆኑ እንደተወሰነ ኢትዮ ነጋሪ ለጉምሩክ ኮሚሽን በተጻፈ ከሰርኩላር ደብዳቤ ላይ ተመልክቷል።

ሚኒስቴሩ በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል ለጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በሙሉ ባስተላለፈው መረጃ መሰረት፣ የሲኖትራክ ካምፓኒው የጥራት ጉድለቶቹን እስኪያስተካክል ድረስ ከግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ምንም ዓይነት የሲኖትራክ ተሽከርካሪ ማስገቢያ ፍቃድ እንደማይሰጥ አስታውቋል።

ከዚህም ባሻገር፣ ሚኒስቴሩ ፊርማና ማህተም በማስመሰል የሲኖትራክ ማስገቢያ ፍቃድ በማዘጋጀት ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚሞክሩ ሰዎች መኖራቸውን መረጃ እንዳገኘ ገልጿል።

ይህን ተከትሎ፣ ከግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ወዲህ በሚኒስቴሩ የተሰጠ ምንም ዓይነት የሲኖትራክ ማስገቢያ ፍቃድ የሌለ መሆኑን በመግለጽ፣ እንዲህ ዓይነት ሰነድ ሲቀርብ አገልግሎት እንዳይሰጥና ጥቆማ እንዲደረግለት ለጉምሩክ ኮሚሽን ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

የጉምሩክ ኮሚሽንም ይህንኑ የሚኒስቴሩን ውሳኔ ለሁሉም የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በማስተላለፍ፣ የሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ አዟል።

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ከሆነ ኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ ከሚበዛባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት።

በኢትዮጵያ ያሉ ተሽከርካሪዎች ቁጥራቸው አነስተኛ የሚባል ቢሆንም በዓመት በአማካኝ 15 ሺህ የትራፊክ አደጋዎች ሲደርሱ 5,000 ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ።

በኢትዮጵያ 1.2 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎች ያሉ ሲሆን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ያህሉ በአዲስ አበባ እና ዙሪያ ከተሞች ያሉ ናቸው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *