ከአዲስ አበባ-ሀርጌሳ- ጅቡቲ የአውቶቡስ ትራንስፖርት ሊጀመር ነው

ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ወራት ወደ ሶማሊላንድ እና ጅቡቲ የአውቶቡስ ትራንስፖርት አገልግሎት የማስጀመር እቅድ እንዳላት ገልጻለች።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ባረኦ ሀሰን መቀመጫውን ኬኒያ ናይሮቢ ያደረገው አቢሲኒያ ሌግዠሪ ኮች ባለቤት እና ማኔጅመንት አባላት ጋር ተወያይተዋል።

አቶ በሪኦ በዚህ ጊዜ እንዳሉት የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚንስቴር በተያዘው በጀት አመት ኬኒያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሌላንድ በየብስ ትራንስፖርት ለማገናኘት እቅድ መያዙን ገልጸዋል።

አገልግሎቱን የመንግስትና ግሉን ዘርፍ ትብብር በማጠናከር በጋራ እንደሚሰራም ሚንስቴር ዴዔታው ተናግረዋል።

በመሆኑም እንደሚኒስቴር መስሪያቤት በሁለቱ ሀገራት በትብብር ለመስራት አስፈላጊ የሆኑ የህግ ማዕቀፎችን የማመቻቸቱን ስራ በትኩረት እንደሚሰራ እና በድርጅቱ በኩል አስፈላጊውን ሂደት አሟልተው እንዲመጡ ከስምምነት መደረሱን ሚንስቴሩ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ያወጣው መግለጫ ያስረዳል።

የአቢሲኒያ ሌግዠሪ ኮች ባለቤት አቶ ሚካኤል ጀምስ በበኩላቸው ድርጅቱ ከኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ወደ አዲስ አበባ በአውቶብስ ተጓዦችን ለማመላለስ ፍላጎቱን እና አገልግሎቱን የሚሰጡ ሀገር አቋራጭ አውቶቢሶችን ማሰባሰብ መጀመሩን ገልጾ ከፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ጋርም በቅንጅት ለመስራት ፍላጎት አሳይቷል ተብሏል።

ባሳለፍነው ሳምንት ከናይሮቢ – አዲስ አበባ በአውቶብስ የሕዝብ ትራንስፖርት መጀመሩ ይታወሳል።

“አቢሲኒያ ሌግዠሪ ኮች’ የተሰኘ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ከኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ወደ አዲስ አበባ በአውቶብስ ተጓዦችን ማመላለስ መጀመሩን በወቅቱ አስታውቆ ነበር።

የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚንስቴር በወቅቱ አዲሱ የአውቶቡስ ትራንስፖርት አገልግሎት ተጀምሯል መባሉ ከእኔ እውቅና ውጪ ማለቱ ይታወሳል።

ጉዳዩ በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል የትብብር ስምምነት መፈራረም፣ ታሪፍ በጋራ መወሰን እና ሌሎች የዲፒሎማሲ ጉዳዮች የሚፈልግ በመሆኑ ከሚመለከተው መንግስታዊ መስሪያቤት ጋር በመተባበር የሚሰራበት መሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *